የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አጠናን

1.ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ማለት መጽሐፍ ቅዱስን ስርዓት በያዘ መንገድ አእምሮን እየተጠቀሙ በመንፈስ ቅዱስ በመደገፍ በዓላማ መመርመር መረዳትና በስራ ላይ ማዋል ነው።የቤረያ አማኞች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው (ሐሥ 17፡11)  

2.የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስፈላጊነት

     

የእግዚአብሔር ቃል እነዲህ ይላል

አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። (2ጢሞ 3፡14-17 )

ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። (ኢሱ 1፡7-8 )

መለኮታዊ የሆነውን የጌታን ቃል ማጥናት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ለናሙና ያሰፈርናቸው እነኚህ ሁለት ክፍሎች አጉልተው ያሳያሉ

አብዛኛው አማኝ በተለይ በአገር ቤት የነበረ የመጽሐፍ ቅዱስን፣ በተለይም የቡድን ጥናትን የተለማመደ ቢሆንም ምናለባት አስፈላጊ ከሆነ በማለት ስለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባጭሩ ከዚያው ያገኘናቸውን ሃሳቦች አሰፍረናቸዋል

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት

1.      የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንረዳለን (መዝ 119:105)

2.      መንፈሳዊ ጉድለታችንን አውቀን ለማስተካከል እንችላለን (ያዕ 1: 22-25)

3.     የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር እናስተውላለን ፣ የሰይጣንንም መንገድ አውቀን እንለያለን (2ቆሮ 2:11)

4.     እግዚአብሔርን እናዳምጣለን፣ ሰው እግዚአብሔርን መስምያ ዋነኛ መንገዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው

5.     የሕይወት መንገዳችንን ያስተካክላል (ኢሱ 1:8)

6.     የዕውነትን ቃል ተሞልተን ለሌሎች ለመናገር እንችላልን

7.     ከህይወታችን የማያስፈልገው ይቆረጣል ያሳድገናል (ኤፈ 6:17 ፣ 1ጴጥ 2:2)

8.     ፍሬያማዎች ያደርገናል (ሉቃ 8:11)

……ወዘተ

3.መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ዘዴ

መጽሐፍ ቅዱስን በሶስት መንገድ ማንበብ እንችላለን

1.አሰሳ (survey)

በአጠቃላይ ዝም ብሎ ማንበብ

የረጅም ምንባብን ዋና ዋና ነገሮች ቶሎ ቶሎ ብሎ ማየት ሲሆን ወጥ የሆነ ሃሳብን ለማግኘትና የመጽሐፍ ቅዱስን አንድነት ለማገናዘብ ይጠቅማል

ለኛውንና  ፊተኛውን ክፍል ገረፍ አድረጎ መመልከት ደግሞ ዳራውን( background) ይሰጠናል

2.ጥናት (study)

ዝርዝሩን በማስተዋል መመልከትና ወደ አነድ ሃሳብ መምጣት::ይህም በሁለት አይነት ይከፈላል

1ኛ.መስተጋብአዊ (inductive)

2ኛ.ሥነ-አመክንዩ (deductive)

(ለዝርዝር ከታች ተመልከት)

3.ጥሞና (meditation)

ቃሉን አንቦ ማሰላሰል

የተወሰነ ክፍል ላይ ያተኮረ ሲሆን ጊዜ ወሰዶ በጸጥታ ቃሉን ማሰላሰል ማውጠንጠን ማንጸባረቅ ራሳችንን መክፍትና ለልባችን የሚናገረንን ማዳመጥ

2.ጥናት (study) በጥቂቱ በዝርዝር

1ኛ.መስተጋብአዊ (inductive)

የተወሰነ ክፍል ወስዶ ዝርዝሮቹን አጥንቶ በዚያ መሠረት ወደ አነድ አጠቃላይ ነጥብ ወይም መደምደሚያ ሃሳብ መድረስ ነው

ምሳሌ ሁሉም ኀጢአትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል(ሮሜ 3፡23)

ሁሉም የሚለው ቃል እኔንም ያጠቃልላል

ሰለዚህ እኔም ኀጢአተኛ ነኝ

መስተጋብአዊ ጥናት 3 ደረጃዎች አሉት

1ኛ.መመልከት (observation)

ምንባቡ በግልጽና በስውር የሚለውን ብቻ መረዳትና መገንዘብ ነው። ቃሉ ምን ይላል? ብሎ መጠየቅ ፣ የራስ የሆነውን ሳይጨምሩ የንባቡን ክፍል ዋና ሃሳብ ለመገንዘብና ለማግኘት ብቻ ጥረት ማድረግ። ማን? ምን? የት? መቼ? እንዴት? ለምን? ስለዚህ-ምን ሆነ? የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ ሃቁን ማጥናት ይቻላል

2ኛ.መተርጎም (interpretation)

ፍቺ መስጠት መተንተንና ቅኔያዊ ንግግሮችን መተርጎም፣ ጠቃሚውን ሃሳብ ለይቶ ማውጣትና ማዛመድ. ለምን የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ጊዜ መልሱን ይሰጠናል

3ኛ.ማዛመድ (application)

ለእኔ ምን ይለኛል? ምን እርምጃ እንድወስድ ይነግረኛል? ብሎ መጠየቅና በስራ ላይ ለማዋል ለራስ አርጎ መቀበል

ይህ ያጠናን ዘዴ በብዛት የተለማደ ሲሆን የግልና የቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ይህንን መንገድ ይከተላል።በዚህ ድረ ገጽ የምናቀረብላችሁ ጥናቶች በዚህ ስር ይጠቃለላሉ።

2ኛ.ሥነ-አመክንዮ (deductive)

አነድ ሀቅን ወይም መደምደሚያ ሃሳብን ለማጽናት ወይም ለማረጋገጥ የተለያዩ ሃሳቡን የሚደግፉ ክፍሎችን ወይም እውነታዎችን በአነድ ላይ መሰብሰብ፣ መመለከትና ማጠናት

ምሳሌ ሀ.ሰው ሁሉ ሃጢያተኛ ነው

የህንን ለማለት የሚያስችለው ወይም የሚደግፋትን ክፍሎች በዝረዝር መልቀምና ማጠናት

ሁሉም ኀጢአትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል (ሮሜ 3፡23)

ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ አስተዋይም የለም እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል …… (ሮሜ 3፡11-…19)

ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው ….. (ሮሜ 3፡20)

ለ.ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞቷል (ሮሜ 5፡8፣1ቆሮ15፡3-6)

በዚህ አዘጋጅተን የምናቀርባቸውን ጥናቶች ለግል ወይንም ለቡድን ጥናት መጠቀም ይላል።ስለዚህም በግል ወይንም በቡድን ጥናት ጊዜ ጥቂት ይረዳሉ ብለን ያሰብናቸውን ሃሳቦች አስፍረናቸዋል

4.የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

ለግል የጥናት ጊዜ የሚረዳ አነስተኛ መመሪያ

ሀ.መጸለይ  እግዚአብሔር የቃሉን ሚሰጥር እንዲገልጽልህ።በራስ ማስተዋልና ጥበብ የጌታ ቃልን በፍጹም መረዳት አይቻልም

ለ.ማስታወሻ ደብተርና ብዕር ለመጻፊያ ለማስታወስና ለሌሎች ለማካፈል እንዲረዳህ

ሐ.መስተጋብአዊ (inductive) ዘዴን በመጠቀም ሶስቱን መሠረታዊ መንገዶች መከተል

1ኛ.መመልከት ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ግምታዊ አሰተሳሰብ አትስጥ ከልሎች ወይም በስብከት የሰማውን ትርጉም ቶሎ ሰጥተህ አትለፍ ፣ ቶሎም በህይወትህ ትርጉም ለመስጠት አትቸኩል በዚህ ክፍል ምን ማለት እንደፈለገ አንብበህ በጥሞና ተረዳ። በሚከትሉት ጠያቄዎች በመደገፍ እውነቱን አስተውል

ባለታሪኮቹ እነማን ናቸው? ምን ተሰራ ምንስ ተደረገ? የት ቦታ በምንስ ሁኔታ? መቼ? እንዴት? ለምንስ? ውጤቱስ ምን ነበር? ምንስ ተፈጠረ?

የምታጠናውን ክፍል ከአውደንባቡ ለይተህ አታውጣው

2ኛ.መተርጎም ፦ምን ማለቱ ነው? 

መፍታት

ምን ማለቱ ነው? የሚለውን በመጠየቅ ፍቺ መስጠት ቃላቶቹን ፣ ሐረጎቹን፣ ቅኔያዊ አነጋገሮችንና ዐረፍተ ነገሮችን መተንተን መዝገበ ቃላት ቢያስፈልግ ተጠቀም

በአሁኑ ጊዜስ ተመሳሳይ የሆነው ምነድነው?

ማዛመድ

ለምን ይህንን ሃሳብ ፣ ሐረግ፣ ቃል ተጠቀመ? ለምንስ ይህንን እዚህ መጥቀስ አስፈለገው? ያሉት የተለያዩ ሃሳቦችስ እነዴት ይዛመዳሉ?

ጠቃሚውን ሃሳብ ማግኘት

ጎልቶ የሚታየውን መንፈሳዊ ሃሳብ ወይም መልዕክት ለይተህ አወጣ

ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋረ መስማማቱን አረጋግጥ

ዋናውን መልዕክት ቸል ብለህ በጥቃቅን ነገሮች ላይ እነዳታተኩር ጥንቃቄ ውሰድ

መንፈሳዊ ያልሆነውን መንፈሳዊ ለማድረግ አትሞክር ያልገባህን ለሌላ ጊዜ ጥናት አስተላለፍ ወይም ሌሎችን በመጠየቅ ተረዳ

3ኛ.በሥራ ላይ ማዋል ፦መጽሐፍ ቅዱስ ለእኔ ምን ይለኛል?

መንፈስ ቅዱስ ጠቃሚውን እውነት እነዲያስረዳህ ጸልይ ልብህንም ከፍተህ አድምጥ በእርሱም ተደገፍ የተማርከውን በስራ ላይ አውል  የህንን ስታደርግ እግዚአብሔር አዳዲስ ነገሮችን ያስተምርሃል፣ ለህይወትህ መመሪያ ታገኛለህ

የተረዳኸውን እውነት ያጸናልሃል።የተማርከው እውነት ዛሬ በተለየ መንገድ ባይናገርህም ሌላ ጊዜ ምንፈስ ቅዱስ ባሰፈላጊው ጊዜ ሲጠቀምበትና ህይወትህን ሲያነጽበት ትመለከታለህ 

5.የቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት

የቡድን ጥናት ጥቅሞች

  1. መጽሐፍ ቅዱስን በሥርዓት የማጥናት ልምድ ይሰጣል
  2. የእግዚአበሔርን ቃል ዕውቀት ያበዛል
  3. በአባላት መካከል የጠበቀ መግባባት፣ መተዋወቅ እና ግንኙነት ይፈጥራል
  4. ሃላፊነት የሚወስዱ ሰዎችን (መሪዎችን) ያበዛል
  5. በግልጽ ለመማማይረዳል
  6. ቃል የማካፈልን ልምድ ይሰጣል፣ ላላመኑት ለመመስከርና ወደ ጌታ ለማምጣት ይረዳል
  7. አነዱ በሌላው ጸጋ የመገልገል ዕድል ያገኛል
  8. የአማኞችን የጸጋ ስጦታ ለመለየት ይረዳል
  9. ሸክም ለመከፋፈል፣ ለመደጋገፍና ለእርስ በርስ እረኝነት ዕድል ይከፍታል

ለቡድን አባላት

  1. ከጌታ ለመማር ልብህን አዘጋጅተህ ና የቤትሥራ ከተሰጠህም በርሱ ላይ ተዘጋጅ
  1. በውይይቱ ለመካፈል፣ ያለህንና የተረዳሀውን ለማካፈል ፈቃደኛ ሁን፣ ሁሉም የሚያበረክተው ነገር አለው፣ እግዚአብሔር በአንተ እነደሚጠቀም አትጠራጠር፣ ከቡድኑ የተለየ ሃሳብ ቢኖርህ አትደንግጥ፣ በዚያ ያለኸው ልትማርና ልትረዳ ነው፣

የኔ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው ብለህም አታስብ፣ ሌሎች የተረዱበትን መንገድ ለመረዳት ሞክር ሌሎች የተረዱበትን መንገድ ለመረዳት ሞክር፣ ሃሳብህን ለመለወጥ ዝግጁ መሆን መልካም ነው

  1. ከመሪው ብቻ አትጠብቅ ፣ መረው ውይይቱን በስርአት ለመምራት እንጂ ለመስበክ ወየም ለማስተማር ቦታው አይደለም
  1. ከሚጠናው ክፍል ወይም ርእስ ውጭ አትወጣ ( አስፈለጊ ሆኖ መሪው ካልፈቀደ በስተቀር)
  1. አብረውህ ለሚያጠኑት የቡድን አባላት ጥንቃቄ አድረግ ፣ በጥሞና ለማድመጥና ለመረዳት ሞክር፣ አይነ አፋሮች እነዳሉ አትዘንጋ
  1. በውይይቱ እኔ ብቻ ልናገር አትበል ለልሎችም እድል ስጥ፣ የሁሉም አሰተዋጽዖ ጥናቱን ፍሬያማ ያደርገዋል
     
  2. ስለሚጠናው ርዕስ ወይም ክፍል፣ አንድቀን በስብከት ወይም ከሌሎች የሰማኸውን ብቻ አታንጸብርቅ፣ ጥያቀዎቹን በመመለስ አዲስ ነገር ለመማር ጥረት አድርግ፣ ቃሉንን ዕለት በዕለት በመመርመር እግዚአብሔር አዲስ ነገርን ያስተምራል
     
  3. እግዚአብሔር ከቃሉ በቀጥታና በቡድኑ አባላት በኩል እነደሚያስተምርህ ተጠባበቅ የተባረከ ጊዜ እነዲሰጣችሁ ጸልይ፣ ጌታን እመን
     

ለጥናቱ መሪ

  1. በሰዓት ጀምረህ በሰዓት ለመጨርስ ሞክር
  1. ለቡድኑ አባላት የጥናቱ ዓላማ በውይይት አብሮ ለመማማር እነጂ የስብከት ወይም የትምህርት ጊዜ እንዳልሆነ አበክረህ አስረዳ
  1. አባላቱ በውይይቱ እንዲካፈሉና ተገቢውን ዝግጅት እነዲያደረጉ አበረታታቸው
  1. በግልና በጋራ የምንባቡ ክፍል እንዲነብብ አድርግ
  1. ጥያቄዎችን ለቡድኑ ማንበብ ወይም በራስህ መንገድ ባጭሩ መግለጽ  ትችላለህ  አላስፈላጊ ማብራርያና ብዙ ሃተታ ግን አሰፈላጊ አይደለም
  1. የመደናገር ወይም ያለመረዳትና ከዓላማው የመሳት አዝማሚያ ካየህ ደግሞ በሚገባ መንገድ ለማስረዳት ሞክር፣ አንተ የጥናቱን አላማና የጥያቄዎቹን ሃሳብ በትክክል ከተረዳህ ይህን ዓይነቱን ችግር በቀላል ታልፈዋለህ

ጥያቄው ድግግሞሽ ወደ ሆነ ሃሳብ ወይም ውይይት የሚያመራ ሆኖ ካገኘኸው አላስፈላጊዎቹን ዝለላቸው

በጥያቄው ያለተጠቀሰ ግን አስፈላጊ የሆነ ተዛማጅ ሃሳብ ከተነሳ ደግሞ ስላልተጠቀሰ ብቻ ውይይቱን አትቅጨው፣ አንተ ያልጠበቀውን መልስ መስጠት ስህተት ወይም ከዓላማ መውጣት አይደለም መናልባት ያላየኸውን ማየት ሊሆን ይችላልና

  1. የጥያቄዎቹን መልስ አነተ አትመልስ ፣ ይህ ዓይነቱ ልምድ አባላቱን እነዲቆጠቡ ሊያደርግ ስለሚችል፣ ካልተረዱት በሌላ መንገድ በመጠየቅ ሃሳቡን እንዲረዱት ለማድረግ ሞክር
  1. ከጥያቄ በላ ያለው የዝምታ ጊዜ አያስደንግጥህ፣ የማሰቢያ ጊዜ አስፈላጊ ነው
  1. ጥያቄውን የሚመልሱት ለአንተ ሳይሆን ለቡድኑ መሆኑን ሁሉም እንዲረዳ አድርግ ሆኖም ሁሉም በሥነ ሥርዓት መደረግ እንዳለበት ግልጽ መሆን አለበት
 

 

 

 

 

 


     

  1. ያልተጠበቁ  ወይም አወዛጋቢ ጥያቄዎች ቢነሱ አያስጨንቁህ፣ ለውይይት ጥሩ አጋጣሚ ሊፈጥሩ ይችላሉ። በውይይት የማይፈታ ከሆነ ብዙ ጊዜ ሳይጠፋ ወደ እሚቀጥለው ሃሳብ ዝለቅ፣ በሚቀጥለው ጥያቄ ካልተምልሰ መልሱን ሌላ ጊዜ ለማግኝት ሞክር፣ አስፈላጊ ከሆነ ባለሞያዎች እንዲመልሱት አድርግ ወይም እነደሁኔታው በተገቢው መንገድ እነዲቛጭ አድርግ
  1. ለጥናቱ ከተመደበው ከምንባብ ክፍል አትውጣ፣ በተቻለ መጠን በክፍሉና በአላማው ላይ እነዲተኮር አድርግ
  1. በተቻለ መጠን ዘና ያለ ሁኔታና እረስ በርስ የመግባባት፣ የመደፋፈርና የመቀባበል ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት አድርግ፣ የሚያፍሩትን አደፋፍር እነጂ አታስገድድ
  1. አነዳነድ ጥያቄዎች የራስን ነገር ከመናገር ለይ ካተኮሩ መልስ ላያገኙ ይችላሉ፣ በዚህ ጊዜ ጥያቄውን አጠቃላይ አድረጎ መጠየቁ ጠቀሜታ አለው  

    ለምሳሌ ምን አይነት ነገሮች ናቸው ይቅር ለማለት የሚያስቸግሩህ? ከሚለው ይለቅ ብዝዎቻችንን ይቅር ለማለት የሚያስቸግሩን ምን ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ? የሚለው ለውይይት ይቀል ይሆናል

  2. የተሰነዘሩትን ሀሳቦች ለመሰብሰብና ውይይቱ ፈር እነዲይዝ ሁሌ ጥረት አድርግ፣ ብዙ ሃሳቦች ሲሰነዘሩና ውይይቱ ሲግል ውሉ ሊጠፋና ግራ የሚጋቡ ሊኖሩ እነደሚችሉ አትዘንጋሆኖም ላለመስበክና ግልጽ የሆነውን በመደጋገም ላለማሰልቸት ተጠንቀቅ

  3. በህይወት ወደ ማዛመዱ ላይ ሁሉም የጥናቱን አላማና የሚጠበቅበትን እነደተረዳ አረጋግጥ
  1. ቡድኑ የተማረውን በህይወት ለመተርጎም እንዲችል እግዚአብሔርን በመጠየቅ በጸሎት አስጨርስ