ወንድም ሰለሞን አየለ (የቤተክርሰቲያኒቱ የሽማግሌዎች ሰብሳቢ)

በመጀመሪያ ራእዩን ለሰጠንና ሥራው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ለረዳን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁን::በተጨማሪም በዚህ ሥራ ላይ በተለያየ መንገድ የተሳተፉትን ወገኖች ሁሉ በቤተክርስቲያን ስም እግዚአብሔር አምላክ እጅግ አብዝቶ ይባርካችሁ እላለሁ::

የወንጌል ሥራ ዘመናትንና ትውልዶችን አልፎ የሚሄድ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው::ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ 28:19 ላይ ለሁላችንም በሰጠን ሃላፊነት መሰረት ይህንን የእግዚአብሔርን ቃል ለብዙዎች እነዲዳርሰ በማድረግ ረገድ በተለያየ ምንገድ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ሃላፊነት እና ግዴታ ነው:: ከዚህም አንጻር ቤተክርሰቲያናችን መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት ለማዳመጥ እነዲቻል አስዋጽኦ ለማድረግ ጌታ ስለረዳት ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ልዑል እግዚአብሔርንም እጅግ አመሰግናለሁ::

 

ወንድም ንጉሱ ጉሌ (የቤተክርሰቲያኒቱ የሽማግሌዎች ምክትል ሰብሳቢ)

ወንጌላችን 40 በሚያህሉ ቅዱሳን አባቶች 1500 ዓመታት ባካተተ ጊዜ ውስጥ በመንፈስ ተነድተው እንደጻፉት የታመነና አንድ ወጥ የሆነ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በክርስቶስ የተገለጠበት ቅዱስ መጽሐፍ ነው::ይህም የመምሥራች ወንጌል አምነው ይድኑ ዘንድ ለተራቡ ሰማያዊ መና፤ ለተጠሙ ደግሞ የሚያረካ የህይወት ውሃ እንደሆነ ለፍጥረት ሁሉ ሊታወጅ ይገባል። በመሆኑም በቀደሙት ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ለእኛ የደረሰውን የወንጌል አደራ ለሚመጣውም ሆነ ለአሁኑ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባን በመረዳት የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም መጽፍ ቅዱስን በንባብ በድረ ገጻችን ላይ በማስቀመጥ በአገራችን ላሉና በአለም ዙሪያ ለተበተኑ ወገኖቻችን ሁሉ በረከት እንዲሆን የታቀደው ወደ ግብ በመድረሱ ደስታችን ታላቅ ነው።ለዚህም የራእዩን ባለቤትና የእወቀት ሁሉ ምነጭ የሆነውን ልዑል አምላካችንን ከልብ እናመሰግናለን።

በመቀጠልም ይህንን ራዕይ በመቀበልና ለቤተክርስቲያን በማቅረብ ቤተክርስቲያን ራዕይዋ  አድርጋ እንድትሰራው ምክናያት የሆነውንና በፍጹም መሰጠት ለእቅዱ መፈጸም ቀዳሚ በመሆን ዋጋ የከፈለውን ወንድማችን ዮንስ ዓሥራትን እግዚአብሔር አብዝቶ ይብርከው እላለሁ። በመጨረሻም ለዚህ ቅዱስ ተግባር እንደ አንድ ሰው በመሆን ዓላማ እንዳለው ሰራዊት ተሰልፋችሁ ዕወቀታችሁን ገንዘባችሁን ጊዜአችሁን በመክፈል ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ሌት ተቀን ሳትታክቱ የለፋችሁትን የፕሮጀክቱ አባላት በሙሉ እግዚአብሔር ከሰማያዊ መዛግብቱ እንደባለጠግነቱ መጠን እንዲሞላባችሁ ምኞቴ ነው።

 

ወንድም ዮሐንስ ዓሥራት (የአይ.ቲ. አገልግሎት ክፍል እና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮጄክት መሪ)

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ ስራ እዚህ ደርሶ ማየቱ በዚህ ፕሮጀክት ለተሰማራንና ንባቦችን በኢንተርኔት በማዳመጥ ለምንገለገል ለሁላችን ታላቅ ደስታና እንዲሁም ታሪካዊ ነገር ነው። ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር ጠቅላይ ጸሐፊ ከአቶ ይልማ ጌታሁን መልእክት እንደተረዳነውም፣ ይህ 1954ቱ የአማርኛ እትም ከወጣ ጀምሮ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በንባብ ሲዘጋጁ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው! በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በአውዲዮ በኢንተርኔት ሲዘጋጅም ምናልባት ይህ የመጀመሪያ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። ይህ ፕሮጀክት በአዲስ ሁኔታ ተዋቅሮ ከተጀመረበት ከሜይ 28/2005 ጀምሮ በሁለት አመት ከአምስተ ወር ጊዜ ውስጥ የብሉይና የሃዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በመላ በድረ ገጻችን ላይ በንባብ ለማውጣት እግዚአብሔር ስላስቻለን እግዚአብሔርን እጅግ እናመሰግናለን። እስከ በ2008 አጋማሽ ድረስ የንባቦቹን ጥራትና ደረጃን የማሻሻልና የተለያዩ የእርማትቶችን የከናውንን ስራ እናካሂዳለን። እግዚአብሔር ቢፈቅድ 2008 ዓ. ም. ውስጥ የመጀመሪያ እትምን (ቨርሽን 1.0ን) በኤም. ፒ. ስሪ አዘጋጅተን ለማሰራጨት ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ፕሮጀክት ከ25 የማያንሱ ወንድሞችና እህቶች ያላሰለሰ ጠረትና የድካም ውጤት እንጂ የጠቂት ሰዎች ስራ አይደለም። ይህ ፕሮጀክት ከግብ እንዲደርስ እራሳችሁን ሳትቆጥቡ ለሰራችሁና በአንድም በሌላም መንገድ ታላቅ አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ የፕሮጀክቱ አባላትና ሌሎችም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሁሉ በኢየሩሳሌም ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትና በራሴም ስም ሆኜ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካችሁ፣ ዋጋችሁ በጌታ ዘንድ ሙሉ ይሁን፣ መስዋእታችሁንም ሁሉ ጌታ ይቀበልላችሁ እለለሁ። (ስለ ፕሮጀክቱ በበለጠ በዝርዝር ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)