የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ( ገላ 5:22)

ብዙዎች የሚጠቅሱት አነድ አባበል አለ

”ጌታ ሆይ ትዕገሥት እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ ግን አሁኑኑ ነው የምፈልገው” ይህ ይመለከትህ ይሆን ?

ትዕግሥት:- የትዕግሥት ፍሬ

ጥናት 1

ርዕስ :- የትዕግሥት ጠቃሚነት

መግቢያ :- ትዕግሥት ማጣት የብዙዎቻችን ችግር ሲሆን ፣ ታጋሽነት የሚጠበቅብን ደግሞ በጣም ትዕግሥት በሚያሳጡ ሁኔታዎች ስናለፍ በመሆኑ ችግሩን ያባብሰዋል ፣ እግዚአብሔርም ህይወታችንን ለማሳደግ ብዙ ትዕግሥት የሚጠይቁ ነገሮችን በመንገዳችን ሊያመጣ ይችላል፣ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የትዕግሥትን ጥቅም ስንመለከት ታጋሽነትን እነድንለማመድ በጣም ያነሳሳናል

  ዓላማ :- ትዕግሥት ልናሳድገው የሚገባ ጠቃሚ ሃብት እንደሆነና በህይወታችንም የሚሰጠን ጥቅም እንዳለ ለመመልከት

የጥናት ክፍል:- መጽሐፈ ምሳሌ (ምሳ) 14:29 ፣ 15:18 ፣ 16:32 ፣ 19:11 ፣ 25:15

  1. ራስህን አስብ፣ በምን ዐይነት ጊዜና በምን በምን ሁኔታዎች ውስጥ ነው ትዕገሥትህን የምታጣው?
  1. በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱትን አምስት ክፍሎች አነብብ::ትዕግሥተኛ ሰው ምን ምን ባህረያት ይታዩበታል?
  1. ትዕግስተኛና ትዕግሥተ-ቢስ (ግልፍተኛ) ሰውን ስታነጻጽር ምን ምን ነገሮችን ታስተውላለህ?
  1. ምሳ 15:18 ስትመልከት ታጋሽነትና ግልፍተኝነት ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያመጣል?

አንተስ ይሄ ነገር በህይወትህ ምን ያህል እውነት ሆኖ አግኝተኸዋል?

  1. በምሳ 16:32 በተጠቀሰው መሠረት ታጋሽ ሰው ከኃያልና ከተማን ከሚወስድ የሚበልጠው ለምንድነው ትላለህ?
  1. 6.ባለህበት አካባቢና በኑሮህ (በትምህረት ቤትህ ፣ በሥራ ቦታህ ፣ በቤትህ ፣ በቤተክርሰቲያን ወዘተ) ትዕግሥት ምን ያህል ጠቃሚነት አለው ትላለህ?
  1. ትዕግሥተኝነትና ትዕግሥተ-ቢስነት በምን መንገዱ ነው ያነድን ሰው ጠቢበኝነት ወይም ሞኝነት (ቂልነት) የሚያመለክቱት?
  1. አነድን ታጋሽ የምትለውን ሰው በሃሳብህ ተመልከት፣ ይህ ሰው በምንስ በሌላ መንገድ ብልህ እነደሆነ ታስተውላለህ?
  1. በትዕግሥትና በገለፍተኝነት(ቁጣ ቁጣ እያለን) የምንናገረው ንግግር በውጤቱ ምን ያህል ልዩነት አለው? (ምሳ 15:18 ፣ 25:15)
  1. ትዕግሥተኛነትና ደንታቢስነት ወይም ምንም ውስጥ አለመግባት (passiveness) ልዩነት አላቸው ወይ? (ምሳ 16:32 ፣ 25:15)

ትዕግሥተኛነትና  ሃይለ-ቢስነትስ (powerlessness) ልዩነታቸው ምንድነው?

  1. በዛሬው ጥናት የተማርከው ትምህርትና ያነበብከው የእግዚአብሔር ቃል አስተሳሰብህንና ህይወትህን በምን መልኩ እንድትቀይር ይጠቁምሃል?
  1. እንደ እግዚአብሔር ቃል መሰረት በትዕግሥት እነድታድግ ጥማት ይኑረህ፣ ጌታም እነዲረዳህ ጸልይ::  

የሚጠና ጥቅሥ :- ገላ 5:22

ጥናት 2

ርዕስ :- ትዕግሥት የመጽናት ኮት

መግቢያ :- በህይወትህ ነገሮች እነዳልጠበከው ሆነውብህ ወደተስፋ መቁረጥ አድርሰውሃ? የአገልግሎትህና የቤተክርስቲያን ድካም የፍሬ-ቢስነት ስሜት እየመጣ ያስቸገርሃል? (ብተወውስ? ምን ለውጥ ያመጣል? ቤ/ክርስቲያን መቼ ነው የምታድገው? የጌታስ ክንድ የሚገለጠው መቼ ነው? የኔስ ህይወት የሚለወጠውና የሚያድገው መቼ ነው? ...ወዘተ ) የሚሉ ይኽን የመሳሰሉ ሌሎች ጥያቄዎች በውስጥህ ይመላለሳሉ?  

ትዕግሥት መጽናት በክርስቲያን ህይወት ውስጥ አሰፈላጊ ሲሆን ዛሬ በየያዕቆብ መልዕክት አማካይነት ስለዚህ ዕውነት እናጠናለን

  ዓላማ :- ተስፋ መቁረጥ ሲደርስብን ፣ ማንም በማይረዳልን ጉዳት ስንጠቃ

እነዲሁም ሌሎች ከባድ ችግሮችና ፈተናዎች ሲገጥሙን መጽናት አስፈላጊ እነደሆነ ለመረዳት

የጥናት ክፍል:- የያዕቆብ መልዕክት 5:7-12

  1. በህይወት ወደ ተስፋ መቁረጥ ያደረሱህን ነገሮች አስብ ፣ ምን ነገሮችና ሁኔታዎች ናቸው?
  1. ያዕቆብ በዚህ ክፍል የመጽናት ምሳሌ አድርጎ የሚጠቅሳቸውን ሶስት ነገሮች ለቅመህ አውጣ 
  1. አንድ ገበሬ በትዕግሥት ስለመጽናት ምን ዓይነት ትምህርት ይሰጠናል?
  1. የጌታን መምጣት እየተጠባበቅን እያለን እርስ በእርሳችን እንድናጉረመርም ሊያደርጉን የሚችሉ ነገሮች ምንና ምን ሊሆኑ ይችላሉ? (አንተ በሌሎች ፣ ሌሎች በአንተ ፣ ሌሎች በሌሎች)
  1. አማኞች እርስ በእርሳችን ማጉረምረም ስንጀምር ውጤቱ ምን ይሆናል?
  1. በቁጥር 9 “እነሆፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል” የሚለው የማስጠንቀቂያ ቃል የማጉረምረምን ችግር በምን መንገድ ሊፈታው ይችላል?
  1. ያዕቆብ የጌታን መምጣት ከቁጥር 7-9 ባለው ክፍል ላይ 3 ጊዜ ጠቅሶታል ፣ የጌታ መምጣት በሁኔታዎች ለመታገሥና ለመጽናት በምን መንገድ ይረዳል ትላለህ?

ይህስ የጌታ መምጣት አንድ ሰው ውን የህይወትና የኑሮ አመለካከት በመለወጥ ረገድ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ያደርጋል?

  1. በአብዛኛው ያገልግሎታቸውን ውጤት በአይናቸው ስላላዩ በጌታ ስም የተናገሩት ነብያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ ሆነው ለመጠቀስ በቅተዋል፣ መልእክታቸውን የእግዚአብሔር ሕዝብ እነኳን ቢቃወመውም አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ችለዋል፣ እነዴት ሊጸኑ ቻሉ ትላለህ?
  1. ኢዮብ የትዕግሥት ምሳሌ ነው (ቁ 10) የኢዮብን ጓደኝች አስብ፣ ጓደኞቻችን በፈተናችን ከማጽናናት ይልቅ የችግር ምንጭ ሊሆኑብን ይችላሉ ወይ? አብራራ

በምንስ መንገድ ለትዕግሥታችንና ለጽናታችን ድጋፍ ሊሆኑን ይችላሉ? እነዲሁም እኛስ ለጓደኞቻችን?

  1. ጌታ እጅግ ርኀሩኀና መሓሪ ነው (ቁ 11) ፣ ይህ የጌታ ባህርይ ለመታገሥና ለመጽናት በምን መንገድ ይረዳናል?
  1. የጥናት ክፈሉን ባጠቃላይ ተመልከት፣ ለአንድ አማኝ በፈተናና በችግር ጸንቶ መቆም ለምን አስፈላጊ ነው?
  1. የያዕቆብ ምክር በህይወትህ በትዕግሥት ለመጽናት ምን ያህል ይጠቅምሃል? 

የሚጠና ጥቅሥ :- የያዕቆብ መልዕክት 1:12

ጥናት 3

ርዕሰ :- የዝግታ አስፈላጊነት

መግቢያ :- ዘመናችን ነገር ሁሉ በጥድፊያ የሚደረግበት ጊዜ ነው:: በመሆኑም በሁኔታዎችና በሰዎች ዝግተኝነት የተነሳ መበሳጨትና መነጫነጭ ብዙ ጊዜ ሲከሰት ይታያል:: በአንጻሩ የክርስትና ህይወት ደግሞ አንዳነድ ነገሮችን በዝግታ፣ ሌሎችን ነገሮች በፍጥነት ማድረግ እንዳለብን ያሳስበናል:: በዕለታዊ ኑሮአችን ዝግታ የሚታይብን እግዚአብሔር በሚፈልገው ቦታ ይሆን? ፈጣን የሆነውስ መሆን በሚገባን ነገር ላይ ይሆን? ዛሬ ስለ ዝግታና ስለ እግዚአበሔር ቃል እናጠናለን  

 ዓላማ :- ለመስማት መፍጠን ለመናገርም መዘግየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት፣ እንዲሁም ቃሉን መስማት ብቻ ሳይሆን የማድረግን አስፈላጊነት ለማስገንዘብ

የጥናት ክፍል:- የያዕቆብ መልዕክት 1:19-27

  1. የሚያደርጉትን የማያውቁ ሰዎች በመንገድህ ላይ ገብተው እንቅፋት ሆነውብህ ያውቃሉ?

  2. በያዕቆብ መልዕክት 1:19-23 ላይ ያሉት 3 አነቀጾች የተያያዘ ሃሳብ አላቸው ለእያነዳነዱ አነቀጽ (paragraph) ርዕስ ለመስጠት በመሞከር የተጠቀሰውን ሃሳብ ለመረዳት ሞክር

  3. በ ቁ.19 ላይ የተጠቀሰው ለመናገርና ለመቆጣት መዘገየት አማኝ ሊኖረው የሚገባ የጽድቅ ባህሪይ ነው::

    ”ለመናገር ከፈጠነ ለመስማት ከዘገየ” ሰው ጋር ስትነጋገር ምን ይሰማሃል?

    -ለመስማት መፍጠን ዝግ እንድትልና ይህንን የጽድቅ ባህሪይ በህይወትህ አነድታሳድግ በምን መንገድ ይረዳል ብለህ ታምናለህ?

  4. በቁጣ ቸኩለህ ወይም በግልፍተኝነት የተናገርክበትን ወይም ሌሎች የተናገሩበትን ጊዜ አስብ:: ውጤቱ ምን ዓይነት ነበር?

  5. ቁጣና ግልፍተኝነት ( ይህ ባህሪይ ባንድ አማኝ አብዝቶ መታየቱ) ውስጣዊ የተደበቀ ስጋዊነትን ምን ያህል ያሳያል?

    - ”ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋት” ሲል ምን ማለት እነደሆን ትረዳለህ?

  6. እንደ ቁ.21 መሠረት ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን ለማስወገድ ቃሉን በትህትና መቀበል ያስፈልጋል:: ቃሉ ግን በህይወታችን የተተከለ ከሆነ ለምን በትህትና እንድንቀበለው አስፈለገ?

  7. ዝግ ያለ መሆን( ወይም መዘግየት) ማለት ምንም እርምጃ አለመውሰድ ማለት አይደለም:: ይልቁንም አርምጃ መውሰድ እንዳለብን ቁ 22-25 እንዴት ያሳስበናል?

  8. በዘመናችን ሰው ማንነቱን ወይም ራሱን በማወቅ እሱነቱን የተሻለ ሰው ለማድረግ ኢንዲችል የተለያዩ ሃይማኖቶችና ባለሙያዎች ምክር ይሰጣሉ::ማንነትን በመረዳትና በማሻሻል አንጻር የእግዚአብሔር ቃል ምን ዓይነት አስተዋጽኦ አለው? ( ቁ 23-25)

  9. በህብረተሰብ ዘንድ ህግ እንደ ጫና ወይም አጋጅ ነገር ተደርጎ የሚቆጠርበት ጊዜ አለ ወይ? ከእግዚአብሔር ህግ ጋር አወዳድረው፣ የእግዚአብሔር ህግ ነጻ ሊያወጣ የሚችለው እነዴት ነው? (ቁ 25)

  10. ራስን ማሳት የሚለው ቃል ሁለት ጊዜ ተጠቅሷል (22፣26) ፣ ይህ ቃል ምን ማለት እንደሆነ ግለጽ?

  11. በቁ.26 ከተጠቀሱት ሶስት ንጹሕ አምልኮዎች (ሃይማኖት ) አንተ የትኞቹን በህይወትህ እየተለማመድክ ነው?

    -         ዛሬ አማኞች (የእግዚአብሔርን ቃል በተመለከተ ) ራሳቸውን የሚያሱትበት መንገድ ምን ምን እንደሆነ ጥቀስ

    -         አንተንስ የሚመለከተህ የትኛው ነው?

    -ማሻሻል ያለብህስ በየትኞቹ አቅጣጫ ነው?

  12. ህይወትህን መርምር፣ እግዚአብሔር በቃሉ ሚናገርህን በጽሞና ለማዳመጥ ጊዜ መውሰድና ህይወትህን በዝግታ መምራት ያስፈልግህ ይሆን?

- በጥንቃቄ ባለማዳመጥ፣ ከችኩልነትና ወይም ከግልፍተኝነት የተነሳ በተደጋጋሚ ነገሮችን ያበላሸህበት ጊዜ አለ? ሰውን የጎዳህበት ጊዜ አለ? ይህ የሆነበትን ዕውነተኛውን የልብህን ምክንያት መርምረህ ለጌታ በማሳየት ጌታ እንዲረዳህ ፀልይ::

የሚጠና ጥቅሥ :- የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና (ያዕ 1: 20)

ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቍጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል( ምሳ 14:29)

ጥናት 4

ርዕስ :- ትዕግሥትና ይቅርታ

መግብያ :- ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ሲሻክር ወይም መሆን እንደሚገባውሳይሆን ሲቀር ነገሩን ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ ምንም እንዳልሆነ አድርጎ ማለፍ ወይም መሸሽ ይቀለናል::ጥሩ ግንኙነት ግን ሁልጊዜ ጥረትን፣ ትዕግሥትንና  ይቅርታ ማድረግን ይጠይቃል

ዓላማ :- በዕርቅ በይቅርታና በትዕግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥናትና ለመረዳት

የጥናት ክፍል :- ማቴ 18:15-35

1.     ሰው ሲጎዳህ (ሲበድልህ) ምላሽህ ምንድን ነው?

2.     በንባብ ክፍላችን ውስጥ የበደለህን ወንድምህን ሲበድልህ ውቀሰው ይላል: ከዚህ ይልቅ የበደለህን ለምን አግልለው አይልም?

3.     አንዳንድ ጊዜ ይህንን ዐይነቱን ድርጊት (መውቀስን) መጋፈጥና ዕርቅን ለመፍጠር ሙከራ ማድረግን የማንወደው ለምንድን ነው?

4.     በ ቁ 15 ላይ ”ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው”ይላል: ጉዳዩን በሁለታችሁ ብቻ መሃል ማድረጉ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

5.     ባይሰማ ደግሞ ሁለት ወይም ሶስት ምስክር ወስዶ ነገሩን ለመጨረስ መሞከሩስ ጥቅሙ ምንድን ነው?

6.     በዳዩ ወንድም ቤተክርስቲያንን ባይሰማት እንደ ”አረመኔና ቀራጭ” ይሁንልህ ይላል: ይህ ማለት ምን ማለት ነው? እነደዚህስ መቆጠሩ ለምንድን ነው?

7.     የኢየሱስ ክርስቶስ በአማኞች መሃል መገኘትና የተመለከትነው የዕርቅ ተግባር ምን ግንኘነት አላቸው?(ቁ 18-20)

8.     ሰባት ጊዜ ይቅርታ ማድረግና እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ይቅርታ ማድረግ ልይነታቸው ምንድን ነው?

9.     ከ ቁ 23 ጀምሮ የተጠቀሰው የንጉሥ ምሳሌ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ትዕግሥትና ምህረት በምን መንገድ ያሳያል?

10. ንጉሡ ዕዳውን የተወለት ባሪያ ለምንድን ነው ባልንጀራውን ባሪያ ሊታገሰውና ሊምረው ያልወደደው?

11. የንጉሡ ምሳሌ የሆነው እግዚአብሔር ዕዳህን ትቶልሀል: በነጻ ይቅርታ ማግኘት በህይወት ላይ ምን ተጽዕኖ (impact) አለው?

12. እግዚአብሔር ፍጹም ይቅርታ እንዳደረገልን ሁሉ እኛም ”ከልብ ይቅር” ልንል ይገባናል (ቁ 35):: ”ከልብ ይቅር” ማለት ምን ማለት ነው?

13. ዛሬ የበደለህንና የጎዳህን አንድ ሰው አስብ: በዛሬው ትምህርት መሰረት ምን እርመጃ ልትወስድ ይገባሃል? አንተ የሚገባህን ልታደርግ ሰትወስን ጌታ ሊረዳህ ዝግጁ ነው:

የሚጠና ጥቅሥ :- ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ

ገሥጸው(ዘሌ 19:17)

ጥናት 5

ርዕስ :- እግዚአብሔርን በትዕግሥት መጠበቅ

መግቢያ :- በህይወታችን በየእለቱ ብዙ ነገሮችን እንጠበቃለን ( ደብዳቤ፣ ውሳኔ፣ ስልክ ወዘተ ) ከሁሉ በላይ ግን ” ጌታ ሆይ እስከ መቼ? ” እያልን መልስ የምንጠብቅባቸው አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎች በህይወታችን ያጋጥሙናል:: በዛሬው ጥናት በዚህ ሁኔታ ያለፈውን ዳዊት የጻፈውን እንመለከታለን

ዓላማ :- በፈተናና በችግር ጊዜ እግዚአብሔርን መጠበቅን ለመማርና ዕርዳታን ለማግኘት አይኖቻችንን አሱ ላይ ብቻ ማድረግ እንዳለብን ለመገነዘብ

የጥናት ክፍል :- መዝ 40 :1-5

  1. በህይወትህ እግዚአብሔርን በመጠበቅ ያለፍክበት ነግር አጋጥሞህ ያውቃል? በዚህ ጊዜ የተሰማህ ምንድን ነው?
  2. ዳዊት እግዚአብሔርን በቆይታ ( በትዕግሥት ) ደጅ እንደጠናው  ይናገራል:: በትዕግሥት መጠበቅና ካለትዕግሥት መጠበቅን አወዳድር::
  3. እግዚአብሔርን በትዕግሥት መጠበቅ ምን ያህል አስቸጋሪ ነው? ለምንስ?
  4. ዳዊት በጥፋት ጉድጓድና በረግረግ ጭቃ ውስጥ ነበር፣ በዚህ ውስጥ ሆኖ ደጅ ሲጠና ምን ሊሰማው እነደሚችል ግለጽ::
  5. ዛሬ ወደ እግዚአብሔር እንድትጮህ የሚያስገድዱህ የጥፋት ጉድጓዶች የምትላቸው ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
  6. ወደ እግዚአብሔር በጮህክበት በእንባ ዘመንህ እንደ ዳዊት እግዚአብሔር ያዘጋጀልህ ” ድንጋይ” ነበርን?
  7. አንድን ነገር የምንጠብቀው ስንታመን ነው እግዚአብሔርን መታመን ማለት ምን ማለት ነው?
  8. ዳዊት በዚህ ክፍል የሰጠው ምስክርነት ምን ያህል አበረታቶሃል? አንተስ እግዚአብሔር ከሁኔታህ ካወጣህ በላ ለሌሎች መመስክርህ ምን ያህል አስፈላጊ ነው ትላለህ? እግዚአብሔር አንተን የረዳበትን ሁኔታ አስብ፣ ይህንንም ለማካፈል ጥረት አድርግ::
  9. በችግር ውሰጥ እርዳታን ከእግዚአብሔር ይልቅ ከሌሎች ለመጠበቅ ውስጣችን የሚገፋፋብን ለምንድን ነው?
  10. በእለታዊ ኑሮአችንና ሁኔታዎቻችን ውስጥ እግዚአብሔር እጁ ከኛ ጋር እንዳለ ማስተዋል አስፈላጊ ነው:: እግዚአብሔር በህይወትህ የሚያደረገልህን በማስተዋል ራስህን ከዳዊት ጋር ( ቁ 5) ምን ያህል ማወዳደር ትችላለህ?
  11. እግዚአብሔር ያደረገልህንና በችግር ውሰጥ የረዳህን አስብ:: በፈተና ውስጥ ካለህ ደግሞ ዳዊት እግዚአብሔርን ከጠበቀ በላ እግዚአብሔር እንደታደገው አንተንም እንደሚታደግ አስብ:: ዳዊት አዲስ ዝማሬን እንዳቀረበ በሚመችህ ምንገድ ለእግዚአብሔር ምስጋናን አቅርብ::

የሚጠና ጥቅሥ :- ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።( ሰቆ 3: 26)

 

ጥናት 6

ርዕስ :- በትዕግሥት መጽናት

መግቢያ :- ተስፋ በሌለበትና መውጫ ቀዳዳ በማይታይበት ሁኔታ ውስጥ መገኘት በሕይወት መኖርን እንዃን ያስጠላል፣ ተስፋ እነዳለው ያወቀ ግን ምንም ዓይነት ሁኔታዎችን ለመቋቋም አቅም ያገኛል: በዚህ ጥናት አማኝ በትዕግሥት እነዲጸና የሚያደርገው ታላቅ ተስፋ ምን እንደሆነ እንመለከታለን

የጥናት ክፍል :- ሮሜ 8: 18 – 27

ዓላማ :- በምድር በሥጋ የምንንኖረው ኑሮ ጊዜያዊ መሆኑን ተገንዝቦ የመጨረሻውን የመዳን ቀን ማሰብና በተስፋ መጠበቅ በመከራና በችግር ውስጥ ቆራጥና ጠንካራ እንድንሆን እነደሚረዳን ለማሳየት

  1. ዛሬ ተስፋ የምታደርጋቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው?
  2. የጥናቱን ክፍል አንብብ:: ሐዋረያው ጳውሎስ ለእኛ ሊገለጥ ያለ ታላቅ ክብር እንዳለ ይጠቅሳል: በማሰከትልስ አሁን ፍጥረት ያለበትን ሁኔታ ምን በማለት ይገልጸዋል? ይህስ ስለ ዓለማችን ሁኔታ ምን ይነግርሃል?
  3. ስለ ደህንነታችን ተስፋ በ ቁ 22 - 25 ላይ ከመጥቀሱ በፊት ስለ ፍጥረት ነፃ መውጣት በ ቁ 18 - 22 ላይ ይገልፃል፣  ጳዉሎስ የፍጥረትን ነጻ መውጣት ቦታ የሰጠው ለምንድን ነው?
  4. በመከራና በፈተና ውስጥ ያለው ስቃይ ከምጥ ስቃይ ጋር መመሰሉ ስለፈተና ምን ዓይነት ገንዛቤ እነዲኖርህ ያደርጋል?
  5. ሐዋረያው ጳውሎስ የሚጠቀምባቸው የሚከተሉት የቤተሰብ ቃላት   የእግዚአብሔር ልጆች ( ቁ 19 ና 21)፣ ምጥ ( ቁ 22)፣ ልጅነት ( ቁ 23) የሚሉት ስለ አማኝ    የአሁንና የወደፊት ሥፍራ ምን ያስገነዝብሃል?
  6. አማኝ በፈተና ውስጥ ሲያልፍ መንፈሳዊው ቤተሰብ ( በጌታ ወንድሞችና እህቶች) ምን ያህል ሊጠቅም ይችላል?
  7. አማኝ ምንም እንኳን አሁንም የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም( ቁ 16) ገና ምን ዓይነት ተስፋ ይጠብቀዋል? (ቁ 23)
  8. አማኝ ክርስቶስ በእርሱ ውስጥ የጀመረውን ሥራ እነዲፈጽም በመጠባበቅ ላይ እያለ የሚቃትተው ( ቁ 23 ) ለምንድን ነው?
  9. ስለ አማኝ ተስፋ በ ቁ 24 - 25 መሠረት የተረዳኸውን ግለጽ
  10. አማኝ ተስፋው እስኪሞላ ድረስ በጉጉትና በትዕግሥት መጠበቅ የሚችለው በምን መንገድ ነው?
  11. በውስጥህ ባለው ትግልና ምጥ መንፈስ እነደሚማልድልህ ማወቅህ በምን መንገድ ይረዳሃል?
  12. እግዚአብሔርን በክርስቶስ በኩል ስላለህ ተስፋ አመስግነው፣ ይህንን ተስፋ በጉጉትና በትዕግሥት መጠበቅ የምትችልበትን ፀጋ እነዲያበዛልህ ጠይቀው

የሚጠና ጥቅስ :- እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፣ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን (ፊል 3 : 20)