ይህ ፕሮጀክት ከ2003 ጀምሮ በልባችን የነበረና በተለያየ መልኩ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን በሜይ 28/2005 በአዲስ ሁኔታ ተዋቅሮ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ድንቅ የእግዚአብሔርን እርዳታና በስራው ላይ የእግዚአብሔርን እጅ አይተናል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዱን ለመግለጽ ያህል፤

1ኛ) የመጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ በአውዲዮ በሲዲ፣ በኤም. ፒ. ስሪና በዲቪዲ የማዘጋጀትን ፈቃድ በደስታ ሰጠን፣

2ኛ) መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉ አንብቦ ለመጨረስ አንድ አመት ተኩል ይፈጃል ብለን ተምነን የነበረ ሲሆን በታላቅ መሰጠትና ትጋት ስራው በመሰራቱ በጁን 2006 በ56 ሳምንት መላ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ስራ (ግርድፍ / ኤዲት ያልተደረገው ንባብ ስራ) ተጠናቀቀ፣

3ኛ) ከኦገስት 2007 እስከ ኦክቶበር 2007 ድረስ በታላቅ ትጋት 60% የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘትን (728 ምእራፎችን) አጠናቀን በኢነተርኔት ላይ ለማውጣት እግዚአብሔር ረድቶናል።

4ኛ) የእርማትና ንባቦችን አስተካክሎና 3 የተለያዩ የኤዲቲንግ ደረጃዎችን አልፎ እያንዳንዱን ምዕራፍ በኢንተርኔት የማውጣቱ ስራ እስከ ዲሴምበር 2007 ይወስዳል ብለን ብንተምንም ኦክቶበር 2007 መጨረሻ ድረስ ስራው ተጠናቋል።

ከዚህ በኋላ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እርማቶችን፣ ማስተካከሎችንና የጥራት ደረጃን ከፍ የማድረግ ስራን የምናካሂድበት ሲሆን ይህ ስራም ቢያንስ ቢያንስ እስከ 2008 አጋማሽ እንደሚቀጥል እንተምናለን። ከዚያም መላ መጽሐፍ ቅዱስን በኤም. ፒ. ስሪ፣ በሲዲና በዲቪዲ የማዘጋጀትን ስራ እናካሂዳለን። መላ መጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ በኤም. ፒ. ስሪ የወሰደው ቦታ 2.8 ጊጋ ባይት ብቻ ስለሆነ፣ ይሄንን በአንድ ዲቪዲ፣ ወይንም በአንድ የኤም. ፒ. ስሪ ማጫወቻ ማጠናቀቅ ይቻላል። እንዲሁም ከአራት እስከ አምስት ሲዲ ውስጥ የሚገባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሞባይል ስልኮች እስከ 4 ጊጋ ባይት ያህል መያዝ የሚችሉ ስለሆነ መላ መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ሞባይልም ጭኖ ማዳመጥ የሚቻልበት ጊዜ ከመቼውም ይልቅ ቅርብ ነው!!! ስለዚህ ጥራትን የማረሙና መጠነኛ የሆነን ደረጃን ከፍ የማድረጉን ስራ ካከናወንን በሗላ በቶሎ መላ መጽሐፍ ቅዱስን (የመጀመሪያውን ቨርሽን) በሲዲ፣ በኤም. ፒ. ስሪና በዲቪዲ ማሰራጨት እንጀምራለን። እግዚአብሔር ቢፈቅድ በ2008 ይሄንን ለማድረግ ተስፋ እናደርጋለን።

 ወደፊት በዚህ ፕሮጀክት ብዙ ራእዮች አሉን። ከእነዚህ ራእዮቻችን መካከል ለመጥቀስ፤

1)     በአኒሜሽን (በዲቪዲ) ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዱን ማዘጋጀት። ይህ ምን ሊመስል እንደሚችል እዚህ ጋር በመጫን (mms://195.35.83.20/SpecialBroadCasts/BibleReading/AnimationDemonstration/) ጥቂት ምሳሌን መመልከት ትችላላችሁ።

2)     ጽሑፍንና ንባብን አብሮ በማድረግ አንዳንዶችን ማዘጋጀት

3)     እግዚአብሔር ቢፈቅድ በኢንተርኔት ንባቦች በቀጥታ ማውረድ (ዳውንሎድ ማድረግን) ማስቻል (ምናልባት በ2009 / በ2010 የሚካሄድ)

4)     ሌሎችም

 በተጨማሪም ተጨባጭ በሆነ መልኩ በዚህ ፕሮጀክት ለመሳተፍ የምትፈልጉ በአይ ቲ. አገልግሎት ኢሜል (it-minstry@j-e-c.org) ወይንም በድረገጻችን ላይ ባለው አስተያየት መስጫ ገጽ እንድታሳውቁንና ጥራትን በመቆጣጠርም ሆነ በሌላ መንገድ እንድታግዙን በትህትና እንጠይቃለን። ለሰራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና ስለድካማችሁም ሥራው ሲጠናቀቅ መላ መጽሐፍ ቅዱስን በኤም. ፒ. ስሪ ልንሸልማችሁ ዝግጁዎች መሆናችንን እንገልጻለን።

 አሁንም ሁልጊዜም ሊረዳን በሚችለው በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎታችሁ እንድታቀርቡንና ይህ ዝግጅት በሁሉ መልኩ ከግብ እንዲደርስ እንድትጸልዩልን በትሕትና እንጠይቃለን።

ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ፡፡

ዮሐንስ ዓሥራት

የአይ. ቲ. አገልግሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮጀክቱ መሪ