ቀን፤ 2006-09-01     

የምእራባውያን አገሮች ሃይማኖት - ሂውማኒዝም

ይሄንን ቪዲዮ በዲቪዲ ማዘዝ ከወደዳችሁ ከዚህ በታች ያሉትን ፎቶዎች በመጫን ሙሉ አድራሻችሁን በኢሜል ብትልኩልን እንልክላችላኩልን።  (ዋጋው መላኪያ ወጪን ሳይጨምር 75 የስዊድን ክሮና SEK  ወይንም $10 የአሜሪካ ዶላር ብቻ ነው)

የዲቪዲው የፊት ገጽ

ማውጫ

 1. መግቢያ
 2. የዚህ ዝግጅት ዓላማ
 3. ሂውማኒዝም ምንድነው?
 4. ሂውማኒስት ማኒፌስቶ ምን ይላል?
 5. ሂውማኒዝም ያይደለው ነገር
 6. ሂውማኒዝም በቀጥታ ከሰይጣን የመነጨ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ
 7. የሂውማኒዝም አደገኛነቱ ምኑ ላይ ነው
 8. እንዴት እንዲህ ሊስፋፋ ቻለ?
 9. መስፋፊያ መንገዶቹና መድረኮቹ
 10. የሂውማኒዝም ሃይማኖት በትምሕርት ቤቶች ውስጥ
 11. ሂውማኒዝምና የግብረሰዶም መንፈስ
 12. ሂውማኒዝምና የፌሚኒዝም መንፈስ
 13. በግልና በቤተክርስቲያን ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን?
 14. አማኝ (ክርስቲያን) ፖለቲካዊ ተጽእኖ ሊያደርግ ይገባዋልን?
 15. የእግዚአብሔር ቃል ስለሂውማኒዝም ምን ይላል?
 16. ሂውማኒዝም ሞራላዊ ስሕተትን ማሳየት የማይቻልበት ሃይማኖት ነው
 17. ሂውማኒዝም አላማ ቢስና ተስፋ ቢስና ሃይማኖት ነው
 18. ማጠቃለያ
 19. ምንጮቻችን

በኢየሩሳሌም ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የታዳጊ ወጣቶች አገልጋዮች የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም(ዶኩሜንታሪ)ን በዲቪዲ ለማግኘትና ለማዘዝ እዚህ ይጫኑ። ዋጋው በስዊድን 75 ክሮነር (10 ዶላር)። የመላኪያ ዋጋውን ጨምረን እንልክላችኋለን።

1.  መግቢያ፤

በአንድም በሌላም ምክንያት ከአገራችን ወጥተን በምእራቡ አለም የምንኖር ሰዎች ሁሉ በብዙ መንገድ እግዚአብሔር ለምእራቡ አለም ባበዛው በረከት አብረን ተጠቃሚዎች ሆነናል። ሕክምናን የማግኘት እድል፣ ስራ ሰርቶ ኑሮን የመግፋት እድል፣ ከጦርነትና ከስደት ተጠብቆ በሰላም የመኖር እድል ልጆቻችንን ያለችግር የማስተማርና ጥሩ ደረጃ የማድረስ እድልንና ሌሎችንም ጠቀሜታዎችን አግኝተናል። 

ሆኖም ልጆቻችን በምእራባውያን የመንግስት ትምሕርት ቤት ውስጥ ምን ምን ገብይተው እንደሚመጡ ቀረብ ብለን ተመልክተን ይሆን? <<ምእራቡ አለም>> ተብሎ የሚጠራው የአለማችን ክፍል ምን አይነት እምነትን እየተለማመደ ይገኛል? ሕብረተሰብ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው ቅስቀሳና የአይምሮ ማጠብ (ብሬንዋሺንግ) ምን ይመስላል? ማስሚዲያው የሚሰብከውን፣ ትምሕርት ቤቶች ዋነኛ መርህና ትክክለኛው አቋም ብለው የያዙትን፣ ፖለቲከኞች የሚመሩበትን በአጠቃላይ  በሕብረተሰብ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ያሉ ተቋሞች የሚያምኑበትንና የሚለማመዱትን ሌላ እንግዳ ሃይማኖትና እምነት በልጆቻችን ውስጥ ለመቅረጽ የሚያደርገውን ጥረት ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

<<ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። እነርሱ ከዓለም ናቸው ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን። >> (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፤4-6)            

 

2.  የዚህ ዝግጅት ዓላማ

 • ስለሂውማኒዝም ምንነትና አደገኛነት ግንዛቤንና መንቃትን ለቤተክርስቲያን ለመስጠት 
 • በዚህ ዘመን በሂውማኒዝም አማካኝነት በስውር እየሰራ ያለውን የሰይጣን አሰራር ለይተን እንድናየው ለማደረግና ለማጋለጥ
 • ሂውማኒዝም የሚያነሳቸውን የሚናቁ የትእቢት አስተሳሰቦችን እንዲሁም ምሽጎችን በእግዚአብሔር ቃል እቃ ጦር ፍጹም ለማፈራረስና ትጥቅ ለማስፈታት 
 • ክርስቲያኖች ለዚህ ጥቃት በእግዚአብሔር ቃል የተሞላ በቂ መልስ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው።
 • በትምሕርት ቤትና በሕብረተሰብ ውስጥ ሂውማኒቶች ለሚያመጧቸው ጥቃቶች በግልና በቤተክርስቲያንም ደረጃ ልንሰጥ የሚንችለውንና የሚገባንን ምላሽ በተመለከተ ሃሳብ መስጠት
 • ከዚህ መረዳት የተነሳ በትምሕርት ቤትና በትምሕርት ተቋሞች አማካኝነት ከሚካሄደው የአይምሮ አጠባ ልጆቻችን የተጠበቁ እንዲሆን ወላጆችን ለማንቃት
 • ቤተክርስቲያን ይሄንን ጥቃት ኮስተር አድርጋ እንድትመለከተውና ትኲረት እንድትሰጠው ለማድረግ
 • ለውይይትና ጥልቀት ላለው ለቀጣይ ጥናት መንደርደሪያ ለመስጠት
 • ይህ ዘገባ የሰይጣንን ክፉ ስራ ብቻ አይተን ተስፋ እንድንቆርጥ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ታላቅ ክንድ ተማምነን እያንዳንዳችን/ቤተክርስቲያን እንድንነሳና በክፉው የተወረሰውን ምድር በማስመለስ በአካባቢያችንንና በምንኖርበትን ምድር ላይ መልካም ተጽእኖ እንድመጣ ለማነሳሳት የታሰበ ዝግጅት ነው።

 

3.  ሂውማኒዝም ምንድነው?

ትርጉሙ፤

ዌብስተር ዲክሽነሪ ሂውማኒዝም የሚለውን ቃል ሲተረጉም

Humanism:  “any system or mode of thought or action in which human interests, values, or dignity predominate” (Webster dictionary)

“…የሰው ዝንባሌ፣ የሰው እምነትና ስብእና ዋነኛ ስፍራውን የያዘበት አስተያየትና ተግባር” ብሎ ይላል።

 

ሂውማኒዝም አራት መሰረታዊ ነገሮችን ይዟል፤

 1. እምነትን በተመለከተ ሴክዩላር ሂውማኒስቶች ኤቲስቶች ናቸው  (እግዚአብሔር መኖሩን ይክዳል፣ ፍጹም ባለማመን ላይ የተመሰረተና ሁሉም ነገር በሳይንስ ማስረዳት ይቻላል፣ ይገባል ብሎ የሚያምን የክህደት ትምህርት ነው)
 2. ፍለስፍናን በተመለከተ ሂውማኒስቶች ናቱራሊስቶች ናቸው። ነባራዊው ነገር ብቻ እንጂ የማይታይ ፈጣሪ የለም። ተፈጥሮ በራሱ ነበረ ይኖራል ብሎ የሚያምን ነው።
 3. ሂውማኒዝም ከዚህ በተረፈ በኤቮሉሽን ሊያምን ግድ አለበት።
 4. ሞራልን በተመለከተ ኤቲካል ሬላቲቪዝም በሚባል ነገር ነው የሚያምኑት። ይህም ማለት ሁሉ ነገር አንጻራዊ ነው እንጂ ፍጹም ትክክል ወይንም ፍጹም ስህተት የሚባል ነገር የለም ብለው ነው የሚያምኑት።

ሂውማኒዝም ምንድነው? ብለን ስንጠይቅና <<እኛ ሂውማኒስት ነን>> የሚሉትን ሰዎች ምን እንደሚያምኑ ቀረብ ብለን ስንመለከት በጣም አስደንጋጭና ለእግዚአብሔር ቃልና እውነት ፍጹም በጠላትነት የሚነሱ አስተሳሰብ እንዳላቸው እንመለከታለን።

መጀመሪያ ደረጃ ሂውማኒዝም ርእዮተ አለም ነው ይላሉ። እንደመነጽር አለምን የምንመለከትበት እምነት ነው ብለው ይላሉ።

First, Secular Humanism is a worldview. That is, it is a set of beliefs through which one interprets all of reality - something like a pair of glasses.

በሁለተኛ ደረጃ ሴክዩላር መባላቸው እንዳያስታችሁ! እራሳቸው ባወጡት ሂውማኒስት ማኒፌስቶ 1ና 2 ላይ እንደሚገልጹት ሂውማኒዝም “ፍልስፍናዊ፣ ሃይማኖታዊና ግብረገባዊ አስተሳሰብ ነው” ብለው ይገልጻሉ።

Second, Secular Humanism is a religious worldview.[2] Do not let the word "secular" mislead you. The Humanists themselves would agree that they adhere to a religious worldview. According to the Humanist Manifestos I & II: Humanism is "a philosophical, religious, and moral point of view."[3] 

 

4. የሂውማኒስተ ማኒፌስቶ ምን እንደሚል እንመልከት

ሂውማኒስቶች <<ዘ ሂውማኒስት ማኒፌስቶ>> የሚባል የእምነት አንቀጻቸውን ያዘለ ሰነድ አላቸው። በዚያም ውስጥ ሂውማኒዝም ምን አይነት እምነት እንደሆነ በግልጽ እንመለከታለን።  ከሚያምኑባቸውና ከሚቆሙባቸው መርሆዎች ውስጥ አንዳንዶቹን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

First: Religious humanists regard the universe as self-existing and not created.

አንደኛ፤ ሃይማኖታዊ ሂውማኒስቶች ዩኒቨርስ (ተፈጥሮ) በራሱ የነበረና ያለ እንደሆነ ያምናሉ።

Second: Humanism believes that man is a part of nature and that he has emerged as the result of a continuous process.

ሁለተኛ፤ ሂውማኒዝም ሰው የተፈጥሮ አንዱ ክፍል እንደሆነና በሂደት አሁን ወዳለበት ደረጃ እንደደረሰ ያምናል።

Third: Holding an organic view of life, humanists find that the traditional dualism of mind and body must be rejected.

ሶስተኛ፤ ህይወት ቁሳዊ ብቻ ነው ብለው ስለሚያምኑ፣ አእምሮና ሰውነት የተለያዩ ናቸው የሚባለውን አስተሳሰብ ፍጹም አይቀበሉትም።

Fourth: Humanism recognizes that man's religious culture and civilization, as clearly depicted by anthropology and history, are the product of a gradual development due to his interaction with his natural environment and with his social heritage. The individual born into a particular culture is largely molded by that culture.

አራተኛ፤ ሂውማኒዝም የሰው ሃይማኖት ባሕልና ስልጣኔ በአንትሮፖሎጂና በታሪክ እንደተነተነው ሰው ከአካባቢው ጋር ካለው ልውውጥ የመነጩ ናቸው ብሎ ያምናል። በአንድ አካባቢ የሚወለድ ግለሰብ በዚያ ባሕል አስተሳሰብ ተቀርጾ ያድጋል ብሎ ያምናል።

Fifth: Humanism asserts that the nature of the universe depicted by modern science makes unacceptable any supernatural or cosmic guarantees of human values. Obviously humanism does not deny the possibility of realities as yet undiscovered, but it does insist that the way to determine the existence and value of any and all realities is by means of intelligent inquiry and by the assessment of their relations to human needs. Religion must formulate its hopes and plans in the light of the scientific spirit and method.

አምስተኛ፤ ሂውማኒዝም የዩኒቨርስ ተፈጥሮ ሳይንስ እንደሚያስረዳው ሌላ አምላክ ወይንም የበላይ ሊኖር ይችላል የሚለውን ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው ያደርገዋል። ምናልባት ወደፊት አንድ ነገር ቢገኝ ልናምን እንችል ይሆናል ብለው ቢሉም ለማንኛውም ነገር ግን መኖርና አለመኖሩን መገምገም የምንችለው በአእምሮ ጥናትና በሳይንስ ብቻ ነው ብሎ ይናገራል። ሃይማኖቶች የሚያምኑትንና ተስፋ የሚያደርጉትን ነገር በሳይንሳዊ ዘዴና በሳይንስ መንፈስ መግለጽ አለባቸው ብሎ ይላል።

Sixth: We are convinced that the time has passed for theism, deism, modernism, and the several varieties of "new thought."

ስድስት፤ በእግዚአብሔርና በአምላክ ወይንም በሌላ የማመን ጊዜ አልፎአል ብሎ ይላል።

Seventh: Religion consists of those actions, purposes, and experiences which are humanly significant. Nothing human is alien to the religious. It includes labor, art, science, philosophy, love, friendship, recreation-all that is in its degree expressive of intelligently satisfying human living. The distinction between the sacred and the secular can no longer be maintained.

ሰባት፤ ሃይማኖት ያለው ለሰው ሲባል ብቻ ነው። ቅዱስና ርኩስ የሚባል ነገር የለም ብሎ ይላል።

Eighth: Religious Humanism considers the complete realization of human personality to be the end of man's life and seeks its development and fulfillment in the here and now. This is the explanation of the humanist's social passion.

ስምንት፤ የምንኖረው በዚህ ብቻ ነውና ሰው የሚፈልገውን ማድረግ ይገባዋል፣ ብሎ ያምናል።

Ninth: In the place of the old attitudes involved in worship and prayer the humanist finds his religious emotions expressed in a heightened sense of personal life and in a co-operative effort to promote social well-being.

Tenth: It follows that there will be no uniquely religious emotions and attitudes of the kind hitherto associated with belief in the supernatural.

አስረኛ፤ ምንም አይነት በእግዚአብሔር ያለ እምነትን የመግለጽ ስሜትን አናሳይም።

 

5.  ሂውማኒዝም ያይደለው ነገር

ሂውማኒቴርያኒዝም (ሰብአዊ ርሕራሄ) ማለት አይደለም! እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ተቃራኒውን እንደሚያደርግ እንመለከታለን። ለምሳሌ፤ በጠና የታመሙ ሰዎች እራሳቸውን እንዲያጠፉ መርዳት (ዩታኒዚያ)፣ ጽንስ ማስወረድን (አቦርሽን) ወ.ዘ.ተ. በጣም ሲያበረታታ ይታያል!!!

 

6.  ሂውማኒዝም በቀጥታ ከሰይጣን የመነጨ እንቅስቃሴና ተጽእኖ ስለመሆኑ

  1. ሂውማኒዝም ከሰይጣን የመነጨ ፍልስፍናና እምነት ሃይማኖትም ለመሆኑ የእግዚአብሔርን መኖር ማስካዱ ብቻ በቂ ማረጋገጫ በሆነም ነበር። በአጠቃላይ በሕብረተሰብ ውስጥ የሞራል መበስበስ እንዲካሄድ የሚያደርገው አስተዋጽኦና በእግዚአብሔር ያለንን እምነት ፍጹም አስጥሎ በሳይንስና በሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ሰው አለምን እንዲገነዘብ ለማድረግ የሚጥር ክፉና ተስፋ ቢስ የተቅበዘበዘ ሕይወት ሰው እንዲኖረው የሚያደርግ አደገኛ መርዝ ነው።
  2. ስለሂውማኒዝም ምንነት ፍለጋ ስናደርግም የሰይጣን አምላኪዎች ቤተክርስቲያን (<<ቸርች ኦፍ ሴታን>>) ድረ ገጽ ላይ ስለሂውማኒዝም በስፋት መገኘቱ አያስደንቅም!

 

7.  የሂውማኒዝም አደገኛነቱ ምን ላይ ነው

a. ሂውማኒዝም ለሞራል መበስበስ ያበረከተው አስተዋጽኦ (የግብረሰዶም መንፈስ፣ ፕሮሚስክዩኢቲ እንዲስፋፋ ማድረጉ ወ.ዘ.ተ.)

b.     የትምሕርት ሲስተምን መቆጣጠሩ

c. ጽንስ ማስወረድን ማበረታታት፣ በጠና የታመሙ ሰዎች እራሳቸውን እንዲያጠፉ መርዳት፣ ወ.ዘ.ተ.

d.     ጸረ-እግዚአብሔርና ከሃዲ ትውልድን አፍርቶአል

e.     በማንኛውም ጊዜ የእግዚአብሔርን እውነት ተቃርኖ የሚነሳና በጠላትነት የሚቆም አስተሳሰብን የተሞላ ነው። ለምሳሌ፣ በስዊድን ያሉ የክርስቲያን ትምሕርት ቤቶችን ቢቻላቸው ለማስቆም አለበለዚያም የድጎማ ገንዘብን በመንፈግ ለመግታት በየጊዜው የሚደረግ ጥረት ይስተዋላል።

f.        <<ኢንቴሊጀንት ዲዛይን>> (ማለትም ሰው ከእርሱ ይልቅ በረቀቀና የበለጠ እውቀት ባለው አንድ አካል ነው የተፈጠረው) የሚባለው ትምሕርት እንዳይሰጥ የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከልክሏል  (http://news.bbc.co.uk/2/hi/americas/4545822.stm)

h.    ከሂውማኒዝም እንቅስቃሴ ዋነኛ አስተዋጽኦዎች አንዱ ጸሎትን ከትምሕርት ቤት ማስቀረት ነበረ። ሂውማኒዝም <<በመንግስት ድጎማ  የሃይማኖት ትምሕርት በትምሕርት ቤቶች ውስጥ መሰጠት የለበትም>> በማለት ስለ ክርስትና ትምህርት እንዳይሰጥ አድርጎአል። ሆኖም በምትኩ የሂውማኒዝም ሃይማኖት ብቻ በስፋትና በሞኖፖል ይሰጣል። ክርስቲያኖች እንግዲያውስ ክርስትና በትምሕርት ቤት ውስጥ ሊሰጥ ካልቻለ ለምን የሂውማኒዝም ሃይማኖት ይሰጣል ሲሉ ላሰሙት ተቃውሞ ሂውማኒስቶች ሃይማኖት እንዳይደሉ አጽንተው ይናገራሉ።

i.        የክርስትና ትምሕርት እንዳይሰጥ አድርጎ በፋንታው ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ አብሮ የሚቀርቡበት የሃይማነቶች ትምሕርት የሚባል ተቋቁሞአል። በዚህ የሃይማኖቶች ትምህርት ክፍለጊዜ የክርስትና ትምሕርትና አቋም እየተንቋሸሸ ሌሎች እምነቶችን እንደሚመረጡ አድርገው አስተማሪዎች ስለሚያቀርቡ፣ ጠለቅ ያለ እምነት የሌላቸውና የእግዚአብሔርን ቃል የማያውቁ ወጣቶች ሳምንት፣ ከሳምንት፣ ወር ከወር፣ አመት ከአመት እግዚአብሔርን ለሚያስክድ ለሂውማኒዝም ሃይማኖት ይዳረጋሉ።

j.        የሕገ መንግስተ ማርቀቅ ስራ ውስጥ የሂውማኒዝም መርሆዎች አይነተኛ ስፍራ ስላገኙ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሌሎችም በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ሁሉ የሚመሩት በዚህ ጸረ-እግዚአብሔር በሆነ መርህ በተሞላ ሃይማኖት ነው

 

8. እንዴት እንዲህ ሊስፋፋ ቻለ?

a.     ቤተክርስቲያን ተኝታ! ትኲረት ሳትሰጠው ቀርታ በስውር ሲደራጅ በመቆየቱ

b.     ቁልፍ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን (ለምሳሌ፤ ትምሕርት ቤት፣ መገናኛ ብዙሃንን (ማስ ሚዲያን)፣ ሕገ መንግስት፣ የፖለቲካውን አለም፤ ወ.ዘ.ተ. በመያዝ በመስራቱ)

c.      የሚቀጥለውን ትውልድ በመድረስ ረጅም ስልት (ስታራተጂ) እንደምንም ብለው የትምሕርት ሚኒስቴር የትምሕርት አሰጣጥ ውስጥ ሂውማኒዝምን በማስገባት በአንድ ትውልድ የዘሩትን በሚቀጥለው ትውልድ ለማጨድ በቅተዋል።

d.     ለሰዎች ልጆች በሚስማማ አታላይ ፍልስፍናቸው፣ በእኩልነት፣ በሰብአዊ ርሕራሄ ወ.ዘ.ተ. ሰበብ በመግባት አጥፊ ትምሕርታቸውን በሎቢ ሊያስፋፉ ችለዋል።

e.     በሕብረተሰብ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ድምጻቸውን በማሰማት፣ በዲቤትና በሌላውም አሬና በመሳተፍ ብዙ ተፎካካሪ የሌለበት  መድረክ ለማግኘት በመቻላቸው ነው።

 

9.  የሂውማኒዝም የመስፋፊያ መንገዶችና መድረኮች

Ø     ትምሕርት ቤት

Ø     በስነ ጽሁፍ ጋዜጣ፣ በኪነቱ ዓለም…..

Ø     በመገናኛ ብዙሃን (ማስሜድያ)

Ø     በፖለቲካው መድረክ

ሂውማኒዝም በፖለቲካው ዓለም (የሴቶች መብት ነው በሚል ሰበብ ጽንስ ማስወረድን (አቦርሽንን) ያበረታታል ፣ ግብረሰዶምነትን የመብትና የእኩልነት ጥያቄ በማድረግ ይሰራል፣)

Ø     የሕጉ መድረክ

Ø     በሐይማኖት ተቋሞች

 

10.  ሂውማኒዝም በትምሕርት ቤቶች ውስጥ፤

ሂውማኒሲቶች ላለፉት ተከታታይ አስር አመታት ፕሮፓጋንዳቸውንና እምነታቸውን በማስተላለፍ በጣም ስኬታማ ሆነዋል። ለዚህ ስኬታቸው ዋነኛ መሳሪያ የሆናቸው በመንግስት ትምሕርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ወጣቶች ላይ ማነጣጠራቸው ነው።

ከዚህ በታች የምንመለከታቸው የሂውማኒስቶች ጽሁፎች በተለይ አሜሪካን የተመለከቱ ሲሆኑ አሜሪካ ለምእራባውያን አገሮች ሞዴልና ምሳሌ እንዲሁም የሂውማኒዝም መናሃሪያና ለመስፋፋቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነች እናስተውላለን። ስለዚህ በሌሎችም ምእራባውያን አገር ተመሳሳይ ክስተቶችን ብናይ ምንም አይደንቅም።

ቻርልስ ኤፍ ፖተር የተባለው “ሂውማኒዝም፤አዲሱ ሃይማኖት” በሚባለው መጽሐፉ ሲጽፍ እንዲህ ሲል ገልጾአል።

“ከሁሉ የሚያይለው የሂውማኒዝም አበር ትምሕርት ቤት ነው፣ ማንኛውም የአሜሪካ ትምሕርት ቤት የሂውማኒዝም ማስተማሪያ ቤት ነው። በሳምንት አንድ ቀን ለአንድ ሰዓት በቁጥር ጥቂት ለሆኑ የወጣቶች የሚሰጥ የሰንበት ትምሕርት በሳምንት አምስተ ቀን በትምሕርት ቤት ለወጣቶች የሚሰጣቸውን የሂውማኒዝም ትምሕርት ይቋቋም ዘንድ እንዴት ይችላል?” ሲል ገልጾአል።

እንዲሁም ጆኒ ጄ ዳንፊ የተባለው ሌላ ሂውናኒስት The Humanist (1983), በተባለው ሽልማት በተሰጠው ድርሰቱ ሲናገር “የሰው ልጆችን ሁሉ የወደፊት እጣ የሚወስነው ጦርነት መካሄድ ያለበትና ድልም ሊገኝበት የሚያስፈልገው በመንግስት ትምሕርት ቤት ክፍሎች ነው። አንዳንድ አስተማሪዎች በትክክል እየተረዱ እንደመጡ የአዲስ እምነት ተከታዮችና አስፋፊዎች ናቸው። የሰብአዊነት ሃይማኖት የተማሪ ቤት ክፍልን በፑልፒት ምትክ በመጠቀም የሂውማኒዝምን ስርዓትና  እምነት በሚያስተምሩት ሁሉ ያስተላልፋሉ። የትምሕርት ቤት ክፍሎች በዱሮውና በአዲሱ መካከል የግጭት ስፍራ ይሆናል ሊሆንም የግድ አለበት። ይህም ማለት በበሰበሰውና ሬሳ በሆነው በክርስትናና ይዞት በሚመጣው ክፋትና ስቃይ መካከልና በአዲሱ በሂውማኒዝም እምነት መካከል የሆነ ግጭት ማለታችን ነው” ብሎ አይን ባወጣ ሁኔታ ሰይጣናዊ አላማውን ገልጾአል።

a.     በስዊድን አንድ መዋእለ ሕጻናት የደረሰው ዘግናኝ ነገር፤ ሴፕቴምበር ሰላሳ 2005 በስዊድን አንድ አሳዛኝና ዘግናኝ ዜና በጋዜጣ ተጽፎ ነበር። አንድ የድራማ ኢንስቲትዩት ተማሪ በትምሕርት ቤቶች ሙሉ ተባባሪነት መዋእለ ሕጻናት ለሚሄዱ ትናንሽ ሕጻናት የፖርኖግራፊ ድርሰት አንብቦላቸው የእነርሱን ምላሽ ለማየት ብሎ ጥናት ያካሂድ ነበረ። ይህ የከነከናቸው ወላጆች ብዙ ድምጽ ስላሰሙና ጋዜጦችም ስለዚህ ሁኔታ ብዙ ስለጻፉ ያ ተማሪ አነስተኛ የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ብቻ ተፈረደበት።

b.     በመካከላችን ያለች አንዲት እህት መዋእለ ሕጻናት የምትሄድን ትንሽ ልጇን በትምሕርት ቤት አስተማሪዋ ሴት ለሴት መጋባት ምንም አይደለም ብላ አስተምራት ልጇ ግራ በመጋባት ይሄንን በተመለከተ እናቷን ትጠይቃለች። ከዚያም ይህች እናት ይህ እግዚአብሔር የማይወደው ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር ነው ብላ ለልጇ አስረዳች። ከዚያም ወደ ልጅቷ ትምሕርት ቤት በመሄድ ልጄን እንዲህ እያላችሁ እንድታስተምሩ አልፈቅድም ብላ ማነጋገር ነበረባት። ይህ ምንም ለውጥ ሳያመጣ በሌላ ጊዜም ይህችው አስተማሪ በድጋሚ ለዚህች ትንሽ ልጅ ስዊድን አገር እንዲህ ማድረግ ይቻላል ብላ ማስተማሯን ቀጠለች።

c.      አንድ የቤተክርስቲያናችን ታዳጊ ወጣት <<ዘ ዳቪንቺ ኮድ>> በመባል የሚጠራውን ጌታ እየሱስንና ክርስትናን የሚሳደበውን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት በጥርጥር ሊያስገባ የሚሞክረውንና በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሰረተ አስመስሎ የወጣውን ልብ ወለድ ፊልም ከክፍል ጓደኞቹ መለየት ባለመቻሉ ሊመለከት ተገዷል።

d.     ጥንቆላን ለሕጻናት የሚያስተዋውቀውንና <<ሃሪ ፖተር>> የተባለውን መጽሐፍ በስፋት በስዊድን ትምሕርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች እንዲያነቡት ይገደዳሉ።

 

11. ሂውማኒዝምና የግብረሰዶም መንፈስ

ግብረ ሰዶምነት ከሞራል ጥያቄነት ወደ መብት ጥያቄነት ተቀይሮ በመብት ሰበብና ማንም ሊጠቃ/ሊገለል አይገባውም በሚል የሂውማኒዝም ፍልስፍና ዛሬ ይህ ጸያፍ እንቅስቃሴ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። ግብረሰዶሞች በየትምህርት ቤቱ እየዞሩ ወንድ ለውንድና ሴት ለሴት መጋባትና በግብረሰዶምነት መመላለስ ምንም የለበትም፣ ኖርማል ነው እያሉ እንዲነዙ በመንግስት ድጎማ ይበረታታሉ። ይህ አይነቱን ነገር ማበረታታት <<ሰው የፈለገበት እንዲደርስና ያለውን ፍላጎት ማሟላት ይገባዋል>> በሚለው የሂውማኒዝም ፍልስፍና ምክንያት ይበረታታል። እንዲሁም ሂውማኒዝም << ርኩስና ቅዱስ የሚባል ነገር የለም>>፣ <<ሁሉም ነገር አንጻራዊ>> የሚል ፈሊጥ አላቸው ነው። ይህም ማለት አንድ ነገር እውነት ነው ብለህ ካመንክ እውነትነቱ ላንተ ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም>> ብለው በሚሉት የተሳሳተና በእግዚአብሔር አለመኖር ላይ የተንተራሰ ርካሽ አስተሳሰብ ምክንያት ግብረሰዶምነትን ሙሉ በሙሉ ያበረታታሉ። ግብረሰዶምነትን መቃወም የሰውን ስብእና እንደመንካትና በሰው ላይ ያለአግባብ እንደመፍረድ እንደሆነ ስለሚቆጥሩ ይሄንን እንቅስቃሴ ለሚጻረሩ ከፍተኛ ተቃውሞ ያሳያሉ።

 

12.  ሂውማኒዝምና የፌሚኒዝም መንፈስ

a.     እንደ ሂውማኒዝም እንደ ግብረሰዶም መንፈስ ለዚህ ዘመንና ለዚህ ትውልድ ሰይጣን ከተላከቸው ከፉ ተጽእኖዎች ፌሚኒዝም ይገኝበታል።

b.     ከሂውማኒዝም ያላነሰ በምእራባውያን ሕብረተሰብ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ካመጡ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው።

c.      አር ኤፍ ኤስ አሌ የተባለው የግብረሰዶሞችን አጀንዳ በሕብረተሰብ ላይ ለማሮጥ የቆመው የስዊድን ድርጅት ፌሚኒዝምን በዋነኛ ደረጃ የያዘና የሚያራምድ እንደሆነ በድረገጹ ላይ አስፍሮት እናገኛለን።

d.     ስለፌሚኒዝም ሰፋ ያለ ገለጻ በዚህ አጋጣሚ ማቅረብ ባንችልም ከሂውማኒዝም ጋር ትልቅ ተባባሪ መንፈስ እንደሆነ ብቻ ገልጸን እናልፈዋለን።

 

13. ሂውማኒዝም በግል ሕይወታችንና በሕብረተሰብ ላይ ያለውን ተጽእኖ ለማገድና ለማፍረስ እያንዳንዳችንና በግልና በቤተክርስቲያን ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን?

a.     በዚህ ዘመን እየሰራ ያለውን መንፈስ አሰራር የሚቀለብስ የእግዚአብሔር እጅ እንዲመጣ በጸሎትና በምልጃ እግዚአብሔርን መማጠን።

b.     በመንፈሳዊ ትጥቅና በጸጋ ስጦታዎች በዚህ አለም ውስጥ ማብራት

c.      ጌታ ለቤተክርስቲያን የሰጠውን የማሰርና የመፍታት ስልጣን ታጥቀን በዚያ መገለጥ

d.     ጥልቅ እውቀትን መገብየትና በአካባቢያችን እየሆኑ ስላሉ ነገሮች ትክክለኛ ግንዛቤን መያዝ

e.     መሆን የማይገባቸዉ ነገሮች በትምህርት ቤት እንዲሁም በሌላ ስፍራ ሲከሰቱ ይህ ለምን ይሆናል ብሎ ጥያቄዎችን በማንሳት ለእግዚአብሄር እውነት መቆም

f.       ልጆቻችንን ከመንግስት ትምሕርት ቤት አውጥቶ ክርስቲያን ትምሕርት ቤት ማስገባት

g.     <<ለዚህ ዓለም መንፈስ አልሰግድም>> የሚል አቋም በወጣቶቻችንና በልጆቻችን እንዲቀረጽ ማድረግ 

h.     በጋዜጣና በሌላም መንገድ ሕብረተሰብ ላይ ተጽእኖ ማምጣት፣ አርቲክል መጻፍ፣ በዲቤቶች ላይ ተሳታፊ

i.        ፖለቲካዊ ተጽእኖ ማምጣት

j.        ልጆችን የማስተማርን ሃላፊነት ቤተክርስቲያን መያዝ ይኖርባታል (የራሳችንን  ትምሕርት ቤቶችን መክፈት፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና ሌሎችንም ተቋሞችን ማቋቋም)

k.      በሕብረተሰብ ውስጥ ድምጽ መሆንና በኢንቴግሪቲ ተቃውሞን ችሎ አካባቢን ለመቀየር ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ

l.        ቤተክርስቲያን በየትምሕርትቤቱ ለእውነት ቆማ የእግዚአብሔር እውነት እንዲነገር በማድረግ የሰይጣንን ውሸት መገልበጥ

m.   ከሌሎች መሰል አቋም ካላቸው አብያተ ክርስቲያኖች ጋር በማበር መስራት

n.     በማስ ሚዲያ መገለጥ፣ በኢንተርኔት፣ በቴሌቪዥን በሳተላይት የእግዚአብሔርን ቃልና እውነት በማቅረብ የሰይጣንን ውሸት በእውነት ማጋለጥ

o.     ሂውማኒዝም በሰፈነባቸው የትምህርት ተቋሞች ለሚማሩ አሞኞች ልዩ ድጋፍና እርዳታ መስጠት

p.     በሰላማዊ ሰልፍ/የድጋፍ ሰልፍ፣ ፔቲሽን፣ ወ.ዘ.ተ. ውስጥ መሳተፍና በሕብረተሰብ ላይ የለውጥ ምክንያት ለመሆን ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ

 

14. አማኝ (ክርስቲያን) ፖለቲካዊ ተጽእኖ ሊያደርግ ይገባዋልን?

a.     <<እናንተ የምድር ጨው ናችሁ። ጨው አልጫ ቢሆን ግን…>>(ማቴ. 5፣13) ጨው ሁለት ሚና አለው። በመጀመሪያ ደረጃ ምግብን ያጣፍጣል በሁለተኛ ደረጃ ምግብ እንዳይበሰብስ ያደርጋል። ማቀዝቀዣ ባልነበረበት ዘመን በስዊድን ጠረፍ ላይ የአሶችን ሆድ እቃ አውጥተው በአሳው ውስጥና ውጪ በጣም ብዙ ጨው በማድረግ አሳው ሳይበላሽ ለወራት እንዲቆይ/እንዲጠበቅ ይደረግ ነበረ። እንዲሁም እኛ የሞራል መበስበስ በዚህ አለም ውስጥ እንዳይዛመት የምናግድ የምድር ጨው ልንሆን ተጠርተናል።

b.     ዮሐንስ መጥምቁ <<ሄሮድያዳ ላንተ ልትሆን አልተፈቀደም…>> (ማር 6፤18) ሲል ሄሮድስን ገስጾአል። በዚህ ዘመን ዮሐንስ መጥምቁ ቢገለጥ በሄሮድስ ላይ የተናገረውን አስመልክቶ ፖለቲካዊ አስተያየት ገልጿል ተብሎ በተተቸ ነበረ። ሆኖም ይህ የእግዚአብሔር ሰው በመንፈስ ቅዱስ የተሞላና የጽድቅ ሰባኪ ሆኖ በዘመኑ የተገለጠ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። ስለዚህም በዚህም ዘመን ቤተክርስቲያን የጽድቅ ሰባኪ ልትሆንና በእግዚአብሔርን ፊት ጽድቅና ሃጢአት የሆነውን ለዚህ አለም ለማሳወቅ ተጠርታለች።

 

15.  የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሂውማኒዝም ምን ይላል?

የሂውማኒዝም መነሻ ንድፈ ሃሳብ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ፍጹም የሚቃረን ነው። ሂውማኒዝም ሰው በውስጡ መልካም ነገር የሞላበት እንደሆነና ቀስ በቀስ ደግሞ በሂደት ወደተሻለ ሰው እንደሚለወጥ ያስተምራል። ስለዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሚል እስኪ እንመልከት።

<<ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው?  እነሆ፥ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።  ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥ ኃጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?>>ኢዮብ 15፤14-16

 

<<እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።>>መዝሙር 51፤5

 

በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና።መክብብ 7፤20፤

 

አንድ ድርሻ ሁሉን እንዲያገኝ ከፀሐይ በታች በተደረገው ሁሉ ይህ ነገር ክፉ ነው፤ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ነው፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ።መክብብ 9፤3፤

 

<<ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወልናል።>> ኢሳ 64፤6

 

“በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና…”ሮሜ 7፤18

ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤  እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥  የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።  አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤  ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።  አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥  እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤  ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤

 

 

 

ሃይማኖታዊ መሰረቶች

ሂውማኒዝም የፍልስፍና ፣ የሃይማኖትና የ ግብረገብ አመለካከት ነው ይባልለታል፡፡ በናቹራሊዝም ፣ ራሽናሊዝምና ሳይንቲዝም ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ነው፡፡ ሂውማኒስቶች ለዚህ ዘመን የሚስማማ ሃይማኖት መቀመር አለብን ብለው ያምናሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በልእለ-ተፈጥሮአዊ መገለጥ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ስራ ላይ የተመሰረተ ፍልስፍናና ታሪካዊ እምነት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጅ ሊያምንበትና ሊያደርገው የሚገባውን ነገር ሊደነግግ የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው ብሎ ያስተምራል፡፡

እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፥ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው እርሱ ያድነናል። ኢሳ 33፤22

 

እግዚአብሄር

·         የለም እንዲሁም ምንም አግባብ የለውም

·         የሰው ምናብ የፈጠረው ተረት ነው

·         ስለዚህ ሂውማኒዝም ከሃዲ /ኤቴይስቲክ/ ነው

 

·         አለ ፣ መኖሩም ለሰው ልጅ ወሳኝነት አለው ፦ የሁሉም ነገሮች መነሻም ነው

·         በተግባሩ ፈጣሪ ፣ ሰጪ፣ ህግን የሚሰጥ፣ ዳኛ፣ አዳኝ፣ ጌታ ነው

·         በባህርይው ታማኝ፣ ሁሉን ቻይ፣ የበላይ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ፍፁም ቸር፣ በግል የሚታወቅ፣ ቅዱስ፣ እውነት ነው

ሁሉ ከእርሱ በእርሱ ለእርሱም ነውና ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን አሜን። ሮሜ 11፤36

ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። ዮሐ 1፤3

 

ተፈጥሮ

ሂውማኒስቶች ጠፈር /ዩኒቨርስ/ በራሱ የሚኖር፣ ስለዚህም ዘላለማዊ ነው ይላሉ፡፡ ህይወት ያላቸው ነገሮች አጋጣሚያዊ በሆነ ዘገምተኛ ለውጥ የእድገት ደረጃቸው  የመጡ ናቸው ይላሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጠፈር /ዩኒቨርስ/ በእግዚአብሄር የተፈጠረና በጊዜ የተወሰነ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ህያዋን ፍጥረታት ደግሞ በእግዚእብሄር የተሰሩ፣ መልካቸውን ጠብቀው የሚኖሩ፣ መሰሎቻቸውን በመተካት የሚራቡ ናቸው፡፡

የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱ ለእርሱ ተፈጥሮአል። ቆላ 1፤15-16

 

ሰው

ሂውማኒስቶች፣ ሰው አካላዊና ጊዜያዊ ብቻ የሆነ፣ በመሰረቱ መልካም ፣ የዘገምተኛ ለውጥ ሂደት ከፍተኛ ደረጃ፣ በራሱ በቂ የሆነ፣ ራሱን ማስተዳደርና ችግሮቹን መፍታት የሚችል፣ የበላይ ስልጣን ያለው እንዲሁም ተጠያቂነቱ ለራሱ ብቻ ነው ይላሉ። እንዲሁም፣ ሰው ዘላለማዊ እጣ ፈንታ የሌለው ሲሆን እግዚአብሄር አለ ብሎ ማመን ደግሞ ኢተአማኒ፣ ብሎም እብደት ነው ይላሉ፡፡

እንደመጽሐፍ ቅዱስ ግን፣ ሰው አካላዊና መንፈሳዊ የሆነ፣ ነጻ የግብረገብ ፈጻሚ፣ እግዚአብሄር በአምሳሉ የፈጠረው ነው። ሰው እግዚአብሄር ከፈጠራቸው ፍጥረት ሁሉ የበላይ፣ ነገር ግን ሃጢአተኛ፣ ከሃጢአት መዳንና የእግዚአብሄር ምሪት የሚያስፈልገው ነው። ሰው ስልጣኑ ውስን፣ ለእግዚአብሄር ተጠሪ የሆነ፣ ዘላለማዊ እጣ ፈንታ ያለው ሲሆን፣ እግዚአብሄር አለ ብሎ ማመን ደግሞ ተአማኒና ጤነኛ በአንጻሩ ግን አለማመን  ስንፍና እንደሆነ ይናገራል፡፡

 

እውቀት

·         ሪያሊቲ /ተጨባጭ እውነት/ ተፈጥሮአዊና አካላዊ ብቻ ነው ተብሎ ስለሚታመን፣ እንዲሁም በሰው ምክኒያታዊ አስተሳሰብና ሳይንሳዊ መንገዶች የሚረጋገጥ ነው ስለሚባል ሃይማኖትም በነዚሁ መንገዶች ሰው ራሱ ሊቀረፀው ይገባል ተብሎ ይታመናል፡፡

·         ሂውማኒዝም በመለኮታዊ መገለጥ ያልተገደበ ነፃ ምርመራን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም የግለሰቦችን የመጨረሻ ራስ ገዝነት ይፈልጋል፡፡

·         ሪያሊቲ /ተጨባጭ እውነት/  አካላዊና መንፈሳዊ፣ እንዲሁም ተፈጥሮአዊና ልእለ-ተፈጥሮአዊ ስለሆነ፣ የሀይማኖት መስራችና ሰጪ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሄር ነው፤ ሪያሊቲን /ተጨባጭ እውነትን/ ሰው ሊያረጋግጥ የሚችለው ተፈጥሮአዊንና መለኮታዊን መገለጥ በመጠቀም ነው፡፡

·         ክርስትና የእግዚአብሄር ቃል እውቀትንና የሰውን ለመለኮታዊ መገለጥ መገዛትን ይጠይቃል፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሄርን ያስገኛል፡፡

 

ዘላለማዊ ህልውና

·         ሂውማኒስቶች ሰው ነፍስ እንዳለው ስለሚክዱ፣ ማናቸውንም የግለሰቦችን ዘላለማዊ እጣ ፈንታም ይክዳሉ፡፡

·         የሂውማኒዝም ሀይማኖት የሰው ማንነት ሙላት እንዲያገኝ ይመኛል፡፡ እንዲሁም መልካሙን ህይወት እዚህ እና አሁን ለማምጣት ይሞክራል፡፡

·         ሰው ከሃጢአት ነፃ ነው ስለሚሉ፣ ሂውማኒስቶች ሰው ያስፈልገዋል ብለው የሚያስቡት ድነት ከጊዜያዊ ችግሮቹ ብቻ ነው፣ እነዚህንም በአጥጋቢ ሁኔታ መፍታት ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡

·         ሂውማኒስቶች የቆዩ ሃይማኖቶች ለሰው ልጅ የማይጠቅሙ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ዘላለማዊ ድነትን ማመን ምናባዊ ብቻ እና ጎጂ እንደሆነም ያስባሉ፡፡

·         ክርስቲያኖች እያንዳነዱ ነፍስ ዘላለማዊ እጣ ፈንታ ይጠብቃቸዋል ብለው ያምናሉ፡፡ መታዘዝ ያላቸው አማኞች ወደ ሰማይ ሲሄዱ በንስሃ ያልተመለሱ ሀጢአተኞች ደግሞ ወደ ገሃነም ይሄዳሉ፡፡

·         ክርስትና ከሰይጣን ጋር ለዘላለም ቅጣትን ከመቀበል፣ ከሀጢአት ድኖ፣ በዚህ አለም በቅድስና መኖርን እና ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም መኖርን ይፈልጋል፡፡

·         ሰው ሀጢአተኛ ስለሆነ ከሃጢአት መዳን ያስፈልገዋል፡፡ በእምነት ኢየሱስ ክርስቶስን በመታዘዝ፣ ሀጢአተኛ የእግዚአብሄርን የማዳን ጸጋ መቀበል ይችላል፡፡

·         ክርስቲያኖች፣ ሂውማኒዝም ልእለ ተፈጥሮን ያለአግባብ በመካድ ሰውን ለዘላለም ፍርድ እንዳይዘጋጅ ያደርጋል ብለው ያምናሉ፡፡

 

ውጤቱ

የሂውማኒስት ሃይማኖት ለሰው የአምላክን ቦታ ሰጥቶ እግዚአብሄርን ይክዳል፡፡

ክርስትና ለእግዚአብሄር ከፍ ያለውን ቦታ በመስጠት ሰውን ትሁት ያደርጋል፡፡

 

 

16. ሂውማኒዝም ሞራላዊ ስሕተትን ማሳየት የማይቻልበት ሃይማኖት ነው፤

ሂውማኒዝም ፍጹም ስህተት ወይንም ፍጹም ትክክል የሚባል ነገር እንደሌለ የሚያምን በመሆኑ አንድ ሰው ስህተት እንደሰራ ማሳየት አይቻልም። የሂውማኒስቶች ሕብረተሰብ ማንንም በስህተቱ ለመውቀስ የማይቻልበትና ፍርድ መስጠት የማይቻልበት ሕብረተሰብ ነው።

 

17. ሂውማኒዝም አላማቢስና ተስፋ ቢስ ሃይማኖት ነው

ሂውማኒዝም ዩኒቨርስ ለምንም አላማ እንደተፈጠረ አያምንም። ትምሕርቱን የሚመሩት በትምሕርት ቤትና በመገናኛ ብዙሃን የሚሰበኩት የኤቮሉሽን ሳይንስ፣ ማቴሪያሊዝምና የሞራል አንጻራዊነት (ሞራል ሬላቲቪዝም) ናቸው። እግዚአብሔርን ከሕብረተሰቡ አውጥተው ያለአላማና ያለግብ እንዲያው እንደ ጉድናንና እንደትል በዚህ ምድር ላይ ለመኖር እንደምንጣጣር ፍጡራን ብቻ ስለሚገልጹ የአንዳንዶች መልካም ተግባርና የሌሎች ክፉ ስራ ምንም ልዩነት የሌላቸው የሕይወት ጥረቶች ናቸው ወደሚልና <<ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ>> ሃሳብ ውስጥ የሚያስገባ ባዶ እምነት ነው። (ምንጭ፤All About GOD Ministries, Inc.
7150 Campus Drive, Suite 320
Colorado Springs, Colorado 80920
719-884-2246
719-884-2247 fax
Email: Questions1.1@AllAboutGOD.com
Website: AllAboutGOD.com)

 

18. ማጠቃለያ

ይህ ዘገባ ስለሂውማኒዝም የመጀመሪያ ግንዛቤን እንዲሰጥ የታቀደ ሲሆን ስለዚህ ጸረ-እግዚአብሔር ሃይማኖትና ትምሕርት የራሳችሁን ጠለቅ ያለ ጥናት እንድታደርጉ ከልብ እናበረታታለን። በዚህ አጋጣሚ ውጊያችን ከደምና ከስጋ ጋር ስላይደለ ከእነዚህ ሁሉ ፍልስፍናዎችና ሃሳቦች በስተኋላ የመሸገውን የሰይጣንን ሃሳብ እንጂ ሰዎችን እንደማንዋጋ ልናስታውስ እንወዳለን። የውጊያውና የድሉ ባለቤት ድል እስኪሰጠን ድረስ በትእግስት መልካሙን የእምነት ገድል በአንድነት ሆነን እንዋጋ! በእግዚአብሔር ጸጋ <<ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለተሰጠ ሃይማኖት እንጋደል!>> እንዲሁም <<ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ!>> እያልን ቅን ልቡናችሁን እናነቃለን። እግዚአብሔር ይባርካችሁ።  

 

19. ምንጮቻችን

  1. Webster's Encyclopedic Unabridged Dictionary of the English Language (New York: Gramercy Books, 1989), p. 691.
  2. For detailed proof that Secular Humanism is a religion, see Clergy in the Classroom: The Religion of Secular Humanism by David A. Noebel, J.F. Baldwin and Kevin Bywater (Manitou Springs, CO: Summit Press, 1995).
  3. Paul Kurtz, in the preface to Humanist Manifestos I & II (Buffalo, NY: Prometheus Books, 1973), p. 3.
  4. Kurtz, Humanist Manifestos I & II, p. 24. Italics added.
  5. "Is Everyone a Humanist?" in The Humanist Alternative, ed. Paul Kurtz (Buffalo: Prometheus Books, 1973), p. 177.
  6. Corliss Lamont, The Philosophy of Humanism (New York: Frederick Ungar Publishing, 1982), p. 145.
  7. Carl Sagan, Cosmos (New York: Random House, 1980), p. 4.
  8. Roy Wood Sellars, "The Humanist Outlook," in The Humanist Alternative, ed. Paul Kurtz (Buffalo: Prometheus, 1973), p. 135.
  9. Julian Huxley, as cited in Roger E. Greely, ed., The Best of Humanism (Buffalo: Prometheus Books, 1988), pp. 194-5.
  10. David A. Noebel, Understanding the Times: The Religious Worldviews of Our Day and the Search for Truth (Eugene, OR: Harvest House, 1991), p. 200.
  11. Max Hocutt, "Toward an Ethic of Mutual Accommodation," in Humanist Ethics, ed. Morris B. Storer (Buffalo: Prometheus Books, 1980), p. 137.
  12. http://www.christiananswers.net/q-sum/sum-r002.html
  13. http://www.biblicaltheism.com/chartreligc.htm
  14. http://www.secular-humanism.com/
  15. http://www.beliefnet.com/story/80/story_8040_1.html
  16. http://www.pearables.com/Newletter8.htm
  17. http://www.j-e-c.org/humanism

 

በኢየሩሳሌም ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የታዳጊ ወጣቶች አገልጋዮች የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም(ዶኩሜንታሪ)ን በዲቪዲ ለማግኘትና ለማዘዝ እዚህ ይጫኑ። ዋጋው በስዊድን 75 ክሮነር (10 ዶላር)። የመላኪያ ዋጋውን ጨምረን እንልክላችኋለን።

በኢየሩሳሌም ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ታዳጊ ወጣቶችን በማስተማር የተሰማራን ወንድሞችና እህቶች