2018-03-05 "...እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ።"
ኦሪት ዘዳግም 4
9-10 እግዚአብሔር፦ ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው።11 እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር፤ እስከ ሰማይም መካከል ድረስ አሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር፤ ጨለማና ደመና ድቅድቅ ጨለማም ነበረ።
29 ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ። 30 ይህም ሁሉ በደረሰብህ ጊዜ፥ ስትጨንቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ። 31 አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም። 32 እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። 33 አንተ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ ሰማህ፥ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ በሕይወት ይኖራልን? 34 አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን?35 እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። 36 ያስተምርህ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማህ በምድርም ላይ ታላቁን እሳት አሳየህ ከእሳትም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። 37-38 አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። 39 እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ።


